mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

የኮምፕዩተር ቫይረስ ምንድነው?

mejemer what is computer virus

ጭሩ የኮምፕዩተር ቫይረስ ማለት ልክ እንደ ማንኛውም ሶፍትዌር ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ባለቸው ሰወች የሚሰራ ሶፍትዌር ነው፡፡ በተለምዶ እንደምናውቀው የጉንፋን ቫይረስ አይደለም፡፡ ቫይረሱ አላማውና አሰራሩ ሌላ ኮምፕዩተር ለመበከል ነው፡፡ ኮምፕዩተሩን ከበከለ በኋላ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ እንዳይሰራ የሚያደርግ ነው፡፡ ወይም ኮምፕዩተሩ ውስጥ ያሉትን የተጠቃሚውን ሰነዶችና የስራ ውጤቶች የሚያበላሽ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ኮምፕዩተሩ ከተጠቃሚው ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡

በእንግሊዘኛውም ቃል ቫይረስ የተባለው ያው በቀላሉ አባባል ኮምፕዩተሩ በቫይረስ ከተበከለ ስለሚያመው መስራት ያቅተዋል ለማለት የተፈለገ ይመስላል፡፡ እንደነገሩ መስራት ቢችልም እንኳን ይደናገረዋል፡፡ ሲከፋ ደግሞ እንደተለመደው ኮምፕዩተሩ የሚሰራ ቢመስልም ተጠቃሚው የሚያደርገውንና ያለውን መደበቅ አይችልም፡፡ ማንኛውም የዊንዶውስ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ለቫይረስ ኢላማ ነው፡፡ የኮምፕዩተር ቫይረስ በግለሰብ፣ በድርጂቶች፣ በመንግስቶች፣ በነጋዴወች ወዘተ ይሰራል፡፡ የኮምፑተር ቫይረስ ለማሰራጨትም ሆነ ለመከላከል ሃገሮችና ድርጅቶች ከፍተኛ ገንዘብ ያወጣሉ፡፡ የሌላውን ስራና ኮምፕዩተር በቫይረስ አበላሽተው ለመደሰትም ቫይረስ የሚሰሩ ግለሰቦች አሉ፡፡ የዚህን ያህል በመጥፎ አስተሳሰብ የተጠመዱ ሰወችም አሉ፡፡ ሁሉም የየራሱ አላማ አለው፡፡ የኮምፕዩተር ቫይረስ ውስብስብ ግን መጠኑ ከሌሎች ሶፍትዌሮች ጋር ሲነጻጻር በጣም ትንሽ ነው፡፡ ብዛቱ ሳይሆን ክብደቱና ይዘቱ ትንሽ ሆኖ ግን አውዳሚ ነው፡፡

የኮምፕዩተር አንቲ-ቫይረስ ምንድነው?

ንቲ-ቫይረስ የተሰራው ያው ቃሉ እንደሚለው የኮምፕዩተር ቫይረስን ለመከላከል ነው፡፡ አሁን ከቅርብ አመታት ወዲህ እራሱ ዊንዶውስ አንቲ-ቫይረስ ለተጠቃሚው በነጻ እንዲጭን ይሰጣል፡፡ ሆኖም ግን ሌሎችም የተሻለ መድሃኒት እኛ ብቻ ነን ብለው የራሳቸውን አንቲ-ቫይረስ የሚሸጡ ነጋዴወች አሉ፡፡ ተጠቃሚው እራሱ የትኛውን አንቲ-ቫይረስ መግዛት እንደሚፈልግ ይወስናል ማለት ነው፡፡ እንደ ጥራቱ እና ተግባሩ ይለያያል፡፡ የነጻ አንቲ ቫይረሶችም አሉ፡፡ በሰፊውና ባይነቱ ለመከላከል ግን የሚገዛው ይሻላል፡፡ ለማንኛውም ዊንዶውስ በየጊዜው ስለሚጠቃ የትኛውም አንቲ-ቫይረስ ቢሆን ሁሉንም ጥቃት አይከላከልም፡፡ አንቲቫይረስ እየሰሩ የሚሸጡ ነጋዴወችም እራሳቸው ቫይረስ ይሰራሉ እየተባለ ይታማሉ፡፡ ቫይረሱንም መድሃኒቱንም እራሳቸው ይሰራሉ ተብለው ይታማሉ፡፡

የኮምፕዩተር የእሳት ግድግዳ ምንድነው?

የፋየርወል ዋናው አላማና ተግባር የማያስፈልግ የኢንተርነት ግንኙነትን መክቶ ለማገድ ነው፡፡ የፋየርወሉ ስራ ልክ በራፍ ላይ እንደቆመ ዘበኛ ያልተጋበዙ እንግዶችን ከልክሎ የተጋበዙትን እንዲገቡ መፍቀድ ጋር ይመሳሰላል፡፡ የዚህ ቲወሪ ትንሽ ውስብስብ ቢሆንም ተጠቃሚው ፋየርወሉን ራውተሩ ላይ ለማዘጋጀት የተወሰኑ ምርጫወች ስለሆኑ ከባድ አይደለም፡፡ ብዙውን ጊዜ እራሱን የቻለ ብቸኛ ፋየርወል የሚጠቀሙት ለምሳሌ መንግስቶች፣ ድርጅቶች፣ ባንኮች ወዘተ ናቸው፡፡ ባሁኑ ጊዜ ግን ግለሰቦችም ይጠቀሙበታል፡፡ ፋየርወል በእንግሊዘኛው እሳት ተከላካይ ግድግዳ እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ ለኮምፕዩተርም መከላከያ የሚሆን ፋየርወል አለ፡፡ እሳት ባይሆንም አደጋ ተከላካይ ለማለት ተፈልጎ ነው፡፡ ፋየርወሉ በቀላሉም ይሆን ተወሳስቦ እንደ አስፈላጊነቱ ይቀመራል፡፡

ቢያንስ ሁለት አይነት ፋየርወሎች አሉ፡፡ አንደኛው ከኦፕሬቲንግ ሲስተሙ ጋር አብሮ እዛው ተጠቃሚው ያገኘዋል፡፡ ለምሳሌ የዊንዶውስ ኮንትሮል ፓነል ላይ ሄዶ ፋየርወሉን እንደ አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ወይም መካከለኛ መጠን ላይ መርጦ መቀስቀስ ይቻላል፡፡ የሚገዙ አንቲቫይረስ ፕሮግራሞችም የራሳቸው ፋየርወል አላቸው፡፡ ሌሎችም ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች ፋየርወል አላቸው፡፡ ሁለተኛው ፋየርወል ደግሞ ከኮምፕዩተሩ ውጭ እራሱን የቻለ ብቸኛ ሃርድዌር ነው፡፡ የራሱ ሶፍትዌር አለው፡፡ አቀማመጡም በተጠቃሚው ኮምፕዩተርና በኢንተርኔት መካከል ነው፡፡ ለምሳሌ ማንኛውም ተጠቃሚ የኢንተርኔት ሽቦ አልባ ራውተር ላይ ገብቶ ፋየርወሉ እንዴት መከላከል እንደሚችል ማስተካከል ይቻላል፡፡ ሽቦ አልባው ራውተሩ ላይ ለመግባት አድራሻው 192.168.x.x ነው፡፡ x ታዲያ እንደ ራውተሩ ሰሪ 0.1 ወይም 1.0 ወይም 1.1 ሊሆን ይችላል፡፡

ክክልኛ አድራሻውን ለማወቅ የራውተሩን መመሪያ ማጣራት ይቻላል፡፡ ይኸ አድራሻ ሽቦ አልባውን ራውተር ለመጠቀም የተለመደ ነው፡፡ ራውተሩ ላይ ገብቶ የሚፈለገውን ነገር ለመከላከልና ለማሳለፍ እንደ ራውተሩ ሰሪና አይነት የሚደረጉት ነገሮች ይለያያሉ፡፡ ለምሳሌ በ 192.168.0.1 ገብቶ ማስተካከል ይቻላል፡፡ ከገቡ በኋላ ከባድ አይደለም፡፡ ከራውተሩ ጋር አብሮ የመጣውን መመሪያ ካዩት እንዴት እንደሚደረግ ያስረዳል፡፡ ወይም ደግሞ ያምራቹ ድረገጽ ገብቶ መረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡ የሽቦ አልባ ራውተሩ አየር ላይ የሚታየው የሚሰየመውና የይለፍ ቃሉም የሚሰራው በ192ቱ አድራሻ ተገብቶ ነው፡፡ ፋየርወሉ ሲዘጋጅ ተጠቃሚው የሚፈልገውን የኢንተርኔት ትራፊክ እንዳይከለክለው ተመካሪ የሚለውን ከመረጠ ችግር የለውም፡፡ ከፍተኛ ደህንነት ወይም ተመሳሳይ የሚለውን ከተመረጠ መሞከርና ከተስማማው በዛው መቀጠል ወይም ወደ ተመካሪ ወደሚለው እንደገና መቀልበስ ይችላል፡፡ ተጠቃሚው ይህንን ሲያደርግ ሌላ ነገር ነካክቶ ከተበላሸበት እራሱ ሃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡ እኔ ፍንጭ ነው የምሰጠው፡፡ ሆኖም ግን ተጠቃሚው ካልሰራለት ወደ መደበኛ አገልግሎቱ ቀልብሶ እንደገና መጀመርና ማስተካከል ከባድ አይደለም፡፡

ሽቦ አልባው ራውተር አየር ላይ ሲታይ ማንም ገብቶ እንዳይጠቀምበት ግን ራውተሩ ላይ ተጠቃሚው ቢያንስ ይለፍ-ቃል ማስገባት አለበት፡፡ አየር ላይ የሚታየውንም ስም ተጠቃሚው መወሰን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ስሙ ለሁሉም ስለሚታይ ከ23 ሰዓት በኋላ ጸጥታን አክብሩ ብሎ ስም መስጠትና መልእክትም ማስተላለፍ ይቻላል፡፡ ትንሽ የተሻለ ደህንነት ለሚፈልግ ሰው ደግሞ የኮምፕዩተሩን ኢንተርኔት ካርድ አድራሻ (ማክ አድራሻ) ራውተሩ ላይ መዝግቦ ካስተዋወቀው ራውተሩ ከሌላ ኮምፕዩተር ጋር ኢንተርኔት እንዳይካፈል ማድረግ ይቻላል፡፡

ማክ አድራሻ ማለት ለአንድ ኤሌክትሮኒክ ካርድ ከአምራቹ የሚሰጠው ልዩ መለያ ቁጥር ነው፡፡ ይኸ መለያ ቁጥር 12 የእንግሊዘኛ ፊዴላትና ቁጥር የያዘ ቅንብር ነው፡፡ እያንዳንዱ የኤለክትሮኒክስ ካርድ እራሱን የቻለ መለያ ማክ አድራሻ አለው፡፡ አድራሻ ይባላል እንጂ ብዙውን ጊዜ እንደ መለያ ስም ሆኖም ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ ኮምፕዩተሩ ዋና ካርድ ላይ የተወተፈው ኢንተርኔት ለምግባት የሚያስችለው ካርድ በእንግሊዘኛ ሌን ካርድ ይባላል፡፡ የዚህ ማክ አድራሻ 000b 489d 7523 ን ይመሳሰላል፡፡ የዚህን አድራሻ ራውተሩ ላይ ተጠቃሚው ከመዘገበው ባካባቢው ያለ ሌላ ሰው ወይም ጎረቤት እንዳይገባ ለማድረግ እንጂ ብዙም ጠቀሜታ የለውም፡፡ ሁል ጊዜ እንግዳ ለጉብኝት ከራሱ ኮምፕዩተር ጋር ሲመጣ ኢንተርኔት ለመግባት ከፈለገ ማክ መመዝገብ ስለሚያስፈልግ ስራ ማብዛት ነው፡፡ ግን ያው ምርጫው አለ፡፡ ራውተሩ እራሱን የቻለ ጠንካራ ይለፍ ቃል ካለው በቂ ነው፡፡ ለማንኛውም ከይለፍ ቃል በተጨማሪ ተጠቃሚው ሌላም የደህንነት እድል እንዳለው ለመጥቀስ ነው፡፡

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!