ልብ ማለትና ትኩረት መስጠት ከማስተዋል ጋር ይመሳሰላል፡፡ ለምሳሌ፤ የሚታየውን ነገር ማየት ብቻ ሳይሆን፤ ልብ ማለት መቻል ሊሆን ይችላል፡፡ መኪና ባጠገባችን ስታልፍ፤ መኪና መሆኗን ብቻ ሳይሆን፤ አይነቷንና ቀለሟን ማስታወስ መቻል አንዱ የማስተዋል ምልክት ነው፡፡ የተባለውን መስማት ብቻ ሳይሆን፤ ምን እንደተባለ ማዳመጥና ማስታወስ መቻል፤ አንዱ የማስተዋል ምልክት ነው፡፡ የሰወችን ችግር ለመረዳት፤ አዕምሯችን ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ፤ አንዱ የማሰተዋል ችሎታ ነው፡፡ ሰወች ሲሳካላቸው አይተን ወይም ሰምተን፤ በጎ ነገር መመኘት፤ የራስን ቀናነት ለማስተዋልና ለመፈተሽ ትክክለኛ ምልክት ነው፡፡
ምልክት የምትባል አስደናቂ ቃል እኔ በጣም እወዳታለሁ፡፡ ምክንያቱም ልብ ማለትና ትኩረት መስጠት ምልክት ከማየት ጋር ይመሳሰላል፡፡ ለምሳሌ ማንበብ ቀላልና በፊዴል የተጻፈ ጽሁፍ ማንበብ ብቻ አይደለም፡፡ የሚታይ ምስል የማሳያ ምልክት ነው፡፡ የሚሰማ ንግግር የታሰበ አቅጣጫ ማሳያ ምልክት ነው፡፡ በመካሄድ ላይ ያለ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ፤ ቀጥሎ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ምልክት ነው፡፡ እነዚህን ምልክቶች ማስተዋል የሚቻለው፤ ልብ ማለትና ትኩረት ማድረግ ስንችል ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሳስበው የኛ ነገር በጣም ያስደነግጠኛል፡፡ አይደለም የሚታይ እና የሚሰማ ምልክት ማንበብ ቀርቶ፤ የተጻፈ የዋጋ ቁጥር አይቶ ዋጋው ስንት ነው ብሎ የሚጠይቅ ህብረተሰብ አለን፡፡
ሁላችንም የምናውቀው አንዳንድ ቀላል የሆነ ተፈጥሯዊ ድግግሞሽ ባጭሩ ልጥቀስ፡፡ የተለመደና የሚደጋገም ምልክት ነው፡፡ ይኸንን ግን ስለምናውቀው፣ ስለሚደጋገምና፣ ስለቆየ ምንም አይመስለንም፡፡ በቃ ተላምደነዋል፡፡ መፍትሄው የሚሰራና የተፈተነ ስለሆነ፤ በየጊዜው እንጠቀምበታለን፡፡ ለምሳሌ ሲርበን ሁላችንም ስለምግብ እናስባለን፡፡ ሲጠማን ሁላችንም የሚጠጣ እንፈልጋለን፡፡ መኪያ እንዳይገጨን እንጠነቀቃለን፡፡ ከበድ ያለ ደመና ካየን፤ ዝናብ መጣል እንደሚችል፤ ማሳያ ምልክት ነው፡፡ ወዲያውኑ፤ ጥላ መዘርጋት ወይም ቤት ውስጥ ገብተን ለመጠለል እናስባለን፡፡ ምጣዱ ከሰማ፤ እንጀራ ለመጋገር፤ መጀመር እንደሚቻል ማሳያ ምልክት ነው፡፡ ጸሀይ ከጠለቀች በኋላ፤ መጨለም እንደሚጀምር ምልክት ማሳያ ነው፡፡ በሚጨልም ጊዜ፤ መብራት ወይም መተኛት እንደሚያስፈልገን እናውቃለን፡፡ ሲነጋ ደግሞ ወደተለያዩ የህይወት እንቅስቃሴወቻችን፤ ለመሰማራት ማሰብ እንጀምራለን፡፡
የእነዚህ ምልክቶች መፍትሄ በየጊዜው ይሰራል፡፡ የተለመደ ክስተት ስለሆነ፤ ለመጥቀስ ያህል ብቻ ብዬ ነው እንጂ ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ በህይወታችን ውስጥ፤ የጋራ የሆነ ምልክትና መፍትሄ ስለሆነ፤ ልብ ማልቱ ግን አይከፋም፡፡ ዋናው ነጥቤ ግን፤ ተፈጥሮ የሆነ ምልክት በምታሳየን ጊዜ፤ ተመሳሳይ መፍትሄ አለን፡፡ ለሁላችንም የሚያስማማ መፍትሄ አለን፡፡ በየጊዜው የሚሰራና አንድ አይነት የሆነ የጋራ መፍትሄ አለን፡፡ በሁላችንም ተፈትኖ ያለፈ ተስማሚ መፍትሄ ነው፡፡ አሁን ቀላሉንና የምናውቀውን በከፊል ካሳየሁ በኋላ ወደ ቀላሉ-ከባድ ሁነታችን ልመልሳችሁ፡፡
ቀላሉ-ከባድ ሁኔታ ግን ተፈጥሯዊ ሳይሆን ሰው ሰራሽ ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ፤ ለምሳሌ ሁላችንም ሰላም እንመኛለን፡፡ መከባበር እንወዳለን፡፡ ማደግ እንፈልጋለን፡፡ በነጻነት መኖር እንፈልጋለን፡፡ በሰላም ለመኖር፣ ለመከባበርና ለማደግ ግን ይሰራሉ ብለን የምንጠቀምባቸው መፍትሄወች እስካሁን ድረስ አልሰሩም፡፡ ምክንያቱም ለሰላም የምንጠቀምበት አስተሳሰብ፣ ለመከባበር የምናሳየው ፍላጎት፣ ለማደግ ያለን አላማ ልክ እንደ ዝናቡ፣ ጥማቱ፣ ምጣዱ፣ ጨለማና ብርሃኑ ምልክት ማንበብ ባለመቻላችን ይመስለኛል፡፡ ቀላሉ-ከባድ ያልሁትም ለዚሁ ነው፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ይኸንን በደንብ ለማስረዳት ሃሳብ አለኝ፡፡ ለማጠቃለል ያህል ልብ ማለትና ትኩረት መስጠት፤ በህይወታችን ውስጥ፤ ሊደርሱ የሚችሉ ምልክቶችን ለማንበብና መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት ማሳየትና መስራት ጋር ይመሳሰላል፡፡ ሰፊ አርዕስት ነው? በቀላሉና ሳይበዛ በክፍል እያደረግሁ የማቅረብ ሃሳብ አለኝ፡፡ መልካም ምሽት!
This policy contains information about your privacy. By posting, you are declaring that you understand this policy:
This policy is subject to change at any time and without notice.
These terms and conditions contain rules about posting comments. By submitting a comment, you are declaring that you agree with these rules:
Failure to comply with these rules may result in being banned from submitting further comments.
These terms and conditions are subject to change at any time and without notice.
የተሰጡ አስተያየቶች