mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

ደባልቄ እና ላዩሽ፤ ልብ ወለድ

mejemer ethiopia listen and ask

ባልቄ አውቶቡስ እየጠበቀ ነው፡፡ እንደ ለመደው ሰው ሁሉ ይገርመኛል ማለት ጀመረ፡፡ በድንገት ቢሆንም፤ ሰላም ለማለት እንዴት ሰው ይቸገራል? ፊት ለፊት ስንተያይ እንተዋወቃለን፡፡ አየሩና ቀኑ ብዙ ያስወራል፡፡ የሚደበቅ ነገር የለው፡፡ የግል ጥያቄ አይደለም፡፡ ታዲያ ችግሩ ምንድነው? ደባልቄ በራሱ ላይ ጥያቄ አበዛበት። የጋራ ችግር ያለባቸው የሚመስሉ እና የሚተክዙ ፊቶች አየ፡፡ የአንዳንዶቹን ፊትና ስሜት ግን መገመት አልቻለም፡፡ ከፍ ብሎ የሚሰማው ጩኸት ግን መንገድ ላይ ካለው ገበያ ብቻ ይመስላል። አውቶቡስ ጠባቂው ሁሉ ጸጥ ብሎ ቆሟል፡፡ በስልክ የተጠመዱት ግን የሆነ ነገር ያያሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ወገኔ በስልክ ተጠምዷል አለ ደባልቄ፡፡ ከዛ ማዶ ይጮሃሉ፡፡ እዚህ ማዶ ደግሞ አንገታቸውን ደፍተዋል አለ፡፡

ባልቄ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ የራሱ ሃሳብ እረፍት ነሳው፡፡ እጁ ላይ ስልክ ያልያዘ ሰው ከታየማ ስራ የፈታ ይመስላል አለ፡፡ የሆነ ሰው ሰላም ለማለት ፈልጎ ተወው፡፡ እንዴ! ሰውየው ምን ነካው? ይሉኛል ብሎ፡፡ ነገር ከመፈለግ የራሱን ስልክ አውጥቶ አንዳች ነገር አያረግም? ስልክ የለውም? ወይስ የሱ ስልክ ስትታይ ታሳፍራለች? ከየት የመጣ ሞኝ ነው እባካችሁ የሚሉት መሰለው፡፡

ደባልቄ ግን አሁንም ሃሳቡን አልጨረሰም፡፡ ህብረተሰቡ በቃ ሰው ሰራሽ ሆነብኝ አለ፡፡ በየቦታው ስልክ፡፡ በግር ለሚያልቅ መንገድ መኪና፡፡ አውቶቡስ እና ታክሲ እያለ በመኪናህ አድርሰኝ፡፡ ድስት እያለ ማይክሮወይቭ፡፡ ሰንደቅ አላማ እያለን ቀለም ማብዛት፡፡ ውኃ እያለን ጨለማ እና ጥማት፡፡ ሰው እያለ እርቀት፡፡ ምግብ እያለ ርሃብ፡፡ ሃሳብ እያለ ድርቀት፡፡ ብልሃት እያለ ሞኝነት፡፡ እንዴት ሳይሆን እሺ፡፡ ማክበር እያለ ማምለክ፡፡ ትምህርት እያለ ስህተት፡፡ ለምን ሳይሆን አሜን፡፡ ወዴት ሳይሆን እሺ፡፡ ያገሬ ሰው ወደት እየሄደ ነው? አለ፡፡

ልጮኸም እንጂ የራሱ ሃሳብ እየተመላለሰ አስቸገረው፡፡ አውቶቡሱም ዘገየበት፡፡ የሚያናግረው ሰው ጠፋ፡፡ የተለየሁ እንጂ እብድ አይደለሁም አለ። የራሱ ሃስብ ፍሰት ፋታ አሳጥቶት ነበርና ጤነኛ መሆኑን በራሱ ለማሳመን ሞከረ። አሁን እንደ መወናጨፍ እና መበሳጨት አደረገው፡፡ እኔን የሚመስል ሰው እንዴት ጠፋ? እያለ፡፡ የጠፋውን ሰው ለመፈለግ ይሁን መፍትሄ ለማግኘት አካባቢውን እየቃኘ ትንሽ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ድንገት ለጊዜው በስልክ ያልተጠመደች ወጣት ፈንጠር ብላ ቆማለች፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ጥለት ያለበት የሚያምር አጭር የአበሻ ቀሚስ ለብሳለች፡፡ ታኮ ጫማ አርጋለች፡፡ አንገቷ ላይ ሸብ ያደረገችው ሻሽ በደረቷ ላይ ወረድ ብሎ ተንጠልጥሏል፡፡ ሻሿ አሳልፎ ቢያሳይም ጡቶቿ ግን አልተጋለጡም፡፡ ጸጉሯም አምላክ የሰጣት ነው፡፡ የተቀባባች አይመስልም። አምሮባት ተረጋግታ ቆማለች፡፡ ግርማ ሞገሷ ግን ያስፈራል፡፡ ገጠሬ አይሏት ከተሜ፡፡ እንደ ደባልቄ ግን በሃሳቧ ሌላ ሰው አትወርፍም።

አካባቢው እሷን ያያል እንጅ እሷ አካባቢውን አታይም። እሷን የሚያያት እንደ ማይጠፋ ስለምታውቅ ምን አለፋት! ሁሉም ነገር በቁጥጥሯ ስር የሆነ ይመስላል። ደባልቄ ግን ይህቺ ልጅ የጎደላት ነገር ቢኖር፤ አንድ ትንሽ ቀይ ውሻ በጠፍር መያዝ እና ለጸሃዩ ነጭ ጥላ ብትዘረጋ ኖሮ ሙሉ ትሆን ነበር አለ በሃሳቡ። በሚያየው ነገር ላይ ሁሉ እንከን አያጣም። የሚሰማውን ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን ማጣራት። የጎደለ ለመሙላት እና የተጣመመ ለማቃናት እርቆ ይኼዳል። ለዚህም ነው ብዙ የኢትዮጵያ ልጆች እሺ ከማለት በፊት ለምን ማለት እንዴት ይቸገራሉ የሚለው።

ባልቄ አሁን መንቀሳቀሴ ጠቀመኝ አለ፡፡ የልጅቷ አቋቋም፣ አለባበስ እና ርጋታዋ ያማልላል፡፡ ከውጯ ይልቅ ልቧን እና ያላወቀውን አስተሳሰቧን ካሁኑ በሃይል ወደደው፡፡ ይቺማ በቃ ዘመናዊ የሆነች ሃገሯን የምትወድ ኢትዮጵያዊት መሆን አለባት አለ፡፡ እንቅስቃሴው የጀግና መሆኑ ተሰምቶት ልጅቷን በጀብድ ያገኛት መሰለው፡፡ ሃሳብ ጨመረችለት፡፡ ነጻነቱ መሰለችው፡፡ የዱሮ አርበኛ አያቶቹ ሁሉ ትዝ አሉት፡፡ የአሁኑ ጨዋታ ግን ጣልያን መግረፍ ሳይሆን አሳ ማጥመድ ነው፡፡ ሲያደንቃት ቆይቶ አንድ ያላወቀው ነገር ትዝ አለው። አቀራረቧ ምን ይመስል ይሆን? ይኸን ያህል አላሳሰበውም፡፡ ወግ ይችልበታል፡፡ ሄዶ ሲያናግራት ግን አፉ እንዳይተባተብ እና ላቡ እንዳይመጣ ብቻ፤ ተረጋጋ! ብሎ እራሱን ነገረው፡፡

ደባልቄ ነገር እና ሰው ቀደም ብሎ ማየት ይችላል፡፡ እስከ ዛሬ ካያቸው ወጣት ሴቶች ሁሉ አንደኛ ሆነችበት፡፡ ምናልባት በጇ ስልክ ስላልያዘች ይሆናል፡፡ ልጅቷ ላይ ያያው ሁሉ አሁንም ብርቅ ሆኖበታል፡፡ የራሱን መስተዎት አገኘ፡፡ ልዩ ሰው፡፡ አሁንም አሁንም ስልክ የሚያወጡትን፤ "እነዚህማ ከሰው የራቁ ናቸው፤" ነው የሚላቸው፡፡ ለማንኛውም እስከ ዛሬ ድረስ ወንዱን፤ ታዲያስ ወንድም ይል ነበር፡፡ ሴቷን ደግሞ ታዲያስ እህት እያለ ነበር ወግ የሚጀምረው፡፡ ስለ አየሩ እና ቀኑ ተጫውቶ ጨርሶ ሲሰናበት ሁሉም ወግ ቀላል ይመስለው ነበር፡፡ ሁል ጊዜ አንድ አይነት ወሬ ስለሚቀድ፡፡ ዛሬ ግን ፈተና የገባ መሰለውና ወሬ ለመቀየር ፈለገ። "እህት አንዳትል አንተ ደንቆሮ! ስለ አየሩ ካወራህ ደግሞ "ጸሃይ እኮ ነው፤ አይታይህም እንዴ? ትልሃለች"" አዲስ ነገር ፍጠር አለው እራሱን። ቀጥ ብሎ ሄዶ እንዲህ አላት፤

ደባልቄ፤ "ታዲያስ አንቺ!" አላት ከዚህ በፊት የሚያውቃት ይመስል እፊቷ ተገትሮ እና ቀርቦ፡፡
ላዩሽ፤ "ምነው ባ'ክህ? እንደዛ ነው ሚባል?" ብላ አፋጠጠችው፡፡
ደባልቄ፤ "እንዴ፤ ዛሬ ገና አየሁሽ! ስምሽን አላውቀው፡፡ ብርቱካን ብልሽ ብርቱካን ካልሆንሽስ?"
ላዩሽ፤ ፈገግ ካለች በኋላ "አይ ምንም አይደል፤ ላዩሽ እባላለሁ" አለችው፡፡ ቀጥ ብሎ መጥቶ ስለቀረባት በድፍረቱ አልከፋትም፡፡ አንዳንዶቹ ደባልቄዎች ወደሷ ሲቀርቡ ወይ እራሳቸውን ያካሉ፤ ወይ አገጫቸውን ይደግፋሉ፤ ወይ ድዳቸው ይዘረጋል፤ ወይ አፋቸው ውስጥ ምንም ነገር ሳይኖር የሆነ ነገር የሚያላምጡ ይመስላል፡፡ ሰልችቷት ነበር፡፡ ታውቀዋለች፡፡ የሚፈልጋት ሳይሆን የሚያከብራት ሰው ትመኛለች፡፡ እሷም እራሷ የዋዛ አይደለችም፡፡ ደባልቄ ግን ደፋርና ፌዘኛ ሆነባት፡፡ የሚፈልጋት ወይስ የሚያከብራት መሆኑን አሁን አላወቀችም፡፡ ሚስጠረኛ እና ደፋር ሆነባት፡፡
ደባልቄ፤ ትክ ብሎ ካያት በኋላ፤ "ስምሽ የጮኸ ነው! እራስሽ ነሽ ያወጣሽው?" አላት፡፡
ላዩሽ፤ "አይ፤ ያኔ የራሴን ስም ለማውጣት አልደረስኩም ነበር፡፡ እናቴ ነች ያወጣችልኝ" አለችው እያሳቀች፡፡

እሱም ስሙን ነገራትና በዛች አጭር ጊዜ ውስጥ እየተሳሳቁ ትንሽ ተጨዋወቱ፡፡ ነጻ መሆኗን በሚያውቀው ዘዴ ካወቀ በኋላ ያንን የማይወደውን ቁጥር መውሰድ ፈለገ፡፡ የሷ ቋንቋና ምልክት ግልጽ ባይሆንም የምትገፋፋው መሰለው፡፡ ድንገት የሷ አውቶቡስ ቀድሞ ደረሰ፡፡ እሱ ግን የሚወደውን ወግ ሲቀድ ቁጥሯን እስካሁን አልጠየቀም ነበር፡፡ ሲተዋወቅ ያልጨበጣትን ሲለያዩ "በይ እሺ የኔ ጎራዳ ቆንጆ መልካም መንገድ" ብሎ ጨብጦ ተሰናበታት፡፡ ወሬውን እንጂ የሰላምታ እጁን መጀመሪያ ሲቀርብ አልዘረጋላትም ነበር፡፡ በቁሙ ፈዘዘ፡፡ ላዩሽም አውቶቡሱ ስለመጣ ጊዜ የላትም፡፡ የሚወዳት ሃገሩ ኢትዮጵያን ተመስላ ከነሰንደቋ ከፊቱ ፈጥና ሄደችበት፡፡ እንዲህ ነው የኛ ጀግና። ውስጡ ቃል አስቦ ድምጽ ግን አልወጣም።

ደባልቄ፤ ላዩሽ ወደ አውቶቡሱ ስትሄድ ገና ፈቅ ከማለቷ ብሽቅ አለ። እሷ የምትይዘው አውቶቡስ እድሜው እና ቀለሙ ደበረው፡፡ "ከርካሳ አውቶቡስ፤ ቀማኝ! ምቀኛ! ይኸን ነበር እሷም ስትጠብቅ የነበረው?" እያለ አውቶቡሱን ሲራገም....
ላዩሽ፤ "ምን አልክ?"
ደባልቄ፤ እንዴት ሰማችኝ ብሎ እሳት የላሰ ጆሮዋን እያደነቀ በድንጋጤ "አይ፤ አንቺን አይደለም" አላት፡፡
ላዩሽ፤ ዘወር አለችና ኮስተር ብላ አይታው ወደ አውቶቡሱ ስትሄድ ቅር ብሏት ነበር። "አንተ ራስህ ከአውቶቡሱ አትሻልም!" አለችው፡፡ ደባልቄ ግን አልሰማትም። ኋላዋን እያገላበጠችና መንቀር መንቀር እያለች ወደ አውቶቡሱ ተራመደች፡፡ የደባልቄ ነገር አደናግሯታል። "አሁን እኮ ከኋላየ እያየኝ ነው'' ብላ አውቶቡሱ ውስጥ ጥልቅ አለች፡፡ እሱ ግን አሁንም አልሰማትም፡፡ ልጅቷ ምን ነካት? እሱ የሚያስበው ስለ ጆሮዋ እሷ የምታስበው ስለ ኋላዋ፡፡ አልተግባቡም፡፡
ደባልቄ፤ "ይቺስ ጆሮዋ ከስልክ የባሰ እሳት የላሰ ነው! ለዚህ እኮ ነው ስልክ ያልያዘችው! የሚቀጥለውን አውቶቡስ ያዢ ብዬ ባዘገያት? ወይ ቀስ ብዬ ትንሽ መንገድ ብዘጋባት? ወይ ብሸኛት ምናለበት ነበር" አለ እንዳትሰማው ቀስ ብሎ፡፡ የማይወደውን ቁጥር ወስዶ በየመንገዱ በስልክ እንደ ሌሎቹ ወሬ ለመቅደድ መሆኑን ሲያስታውስ ደግሞ በራሱ ሃሳብ ደነገጠ፡፡

ዩሽ፤ አውቶቡስ ውስጥ ገብታ ቁጭ እንዳለች ተቆጭታ ''ኡፍፍፍፍ እንደ ዛሬ ተደብሬ አላውቅም! አለች። እኔ እራሴ የሱን ስልክ ብጠይቀው ኖሮ.......ማለት ጀመረች"፡፡ ልጅቷን ምን ነካት? ለመሆኑ እሱ ስልኩን ለሷ መስጠት መፈለጉን እንዴት አወቀች? እሱ እንደሆነ አንዳንድ ጊዜ ካልተሳሳተ በስተቀር፤ ወንድ ለሴት ስልክ አይሰጥም ይላል፡፡ እሷ ይኸን አታውቅም? ሴቶች አይደውሉም። ስልክ ቢሰጣትም የቁጥር ፍላጎቷን ለማርካት ካልሆነ በስተቀር እንደማትደውል እራሷ አሳምራ ታውቃለች፡፡

ደባልቄ፤ "ጎረቤቴ አይደለች፡፡ ሁለተኛ አላገኛት፡፡ ሌላ ጊዜ እንዴት አገኛታለሁ?" ቀጠለና የዛሬው ገጠመኝ አንድ ዘፈን አስታወሰው፡፡
የሰማዩ ጌታ የምድሩ ባለቤት፣
የምወዳትን ልጅ አርግልኝ ጎረቤት፡፡ የሚለውን፤
ከዛም ላዩሽን የወሰደበት ምቀኛ አውቶቡስ ከአይኑ ሲጠፋለት፤
ፍቅር፣ ፍቅር፣
በቃ ሄደች ይቅር፡፡
አለ ላዩሽ እንዳትሰማው ቀስ ብሎ። የላዩሽ ጆሮ አይታመንም፡፡ ኢትዮጵያን ተመስላ መንፈስ የሆነችበት መሰለው፡፡ በአስታወሰው ዘፈን እና አሁን በፈጠራት ግጥም ፍርፍር ብሎ እንደ ሞኝ ሲስቅ፤ ሲጠብቅ የነበረው አውቶቡስ መጣና ይዞት ጥርግ አለ፡፡ ደባልቄ ሌላ ጊዜ ላዩሽን እንዴት ማግኘት እንደሚችል እዛው አውቶቡስ ውስጥ እያለ ማቀድ ጀመረ፡፡ ድንገት ሳያስበው በንዴት ጮኸና "አገኛታለሁ" አለ፡፡ አውቶቡስ ውስጥ የነበሩት ባለስልኮች ጩኸቱ አቋረጣቸው፡፡ እነሱ ግን በዙሪያቸው ምን እንደሆነ ማወቅ አይፈልጉም፡፡ ደንዝዘዋል። እንደገና አንገታቸውን ወደ ስልካቸው ደፉት፡፡ ደባልቄም ላዩሽን የቀማው አውቶቡስ ቁጥር አይጠፋውም፡፡ እሱን ይዞ ሌላ ጊዜ ለመዞር ወሰነ፡፡ ከተሳካለት!

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

Avatar
New
Haronsays...

mirt hasb nw

Admin:

ስለወደዱት ደስ ብሎኛል አመሰግናለሁ //ፋተ 

Avatar
New
Habtamusays...

Astmari hasab nw ena be gela betam des belogn des malet becha and negr awqabtaklew

Admin:

ልክ ነው ከሃገር ጋር የተያያዘ የሆነ መልዕክት ይኖረዋል። አመሰግናለሁ! //ፋተ 

Avatar
New
Semahagnsays...

It is a nice one Fantaw. My comment is if you specify the name of the characters rather than using a general pronoun( he and she), it will be easy to remember and to tell the stories for others. I appreciate you effort.

Admin:

በጣም ጥሩ ሃሳብ ነው ሰማሃኝ፡፡ በሚመች ስም አስተካክያለሁ፡፡ ለምክርዎ አመሰግናለሁ! //ፋተ 

Avatar
New
Addissays...

ሰላም ፋነታሁን በጣም ጥሩ ልቦለድ ነው እናም ክፍል ሁለትን እንጠብቃለን

Admin:

አመሰግናለሁ አዲስ! 

እዚህ ላይ ክፍል ሁለት እንዲኖር አላቀድኩም፡፡ ግን ምን ይታወቃል? የሆነ ነግር አያይዠ እጽፍ ይሆናል፡፡ //ፋተ