mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

የአስተሳሰብ ጀግና ማለት ምንድነው?

mejemer ethiopia what is hero

አስተሳሰብ ጀግና ስል አንድ ሰው ባመነበት ነገር ላይ ገትሮ ሲይዝ ለማለት ነው፡፡ ባጭሩ ያስተሳሰብ ጀግና ማለት አንድ ሰው ያሰበውን ለማሳካት በቀጣይነት የሚያደርገው ሃሳባዊ ትግልና ጥልቅ ፍለጎት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በሃሳቡ ከጊዜና ከሁኔታ ጋር ፊት አድርጎ ይሄዳል እንጅ አይቀያየርም፡፡ መሰረታዊ ሃሳብና እምነቱ አንድ አይነት ነው፡፡ ምክንያቱም አስፈላጊ ነኝ ብሎ ያስባል፡፡ በራሱ ይተማመናል፡፡ ማንኛውም ሰው ከተለማመደ በራሱ መተማመን ይችላል፡፡ ይኸ ጀግናዊ ጥልቅ ፍላጎትና አስተሳሰብ ለመልካም ወይም ለመጥፎ አላማ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ግን እዚህ ለማስረዳት የሚመቸኝ ስለ ጥሩ አላማ አስተሳሰብ ነው፡፡ በሰፊው እንደምናውቀው፤ ወኔ ወይም ጀግና ማለት ጦር ሜዳ ሄዶ ጀብዱ መስራት ብቻ አይደለም፡፡ ተናዶ ጠረጴዛ መምታት አይደለም፡፡ ሰወችን ልክ ልካቸውን ነግሮ ቲፎዞ ለማግኘትና ለጊዜው ለማሸነፍ አይደለም፡፡

አሁን አንዳንድ ተጨባጭ ነገሮችን ልጥቀስ፡፡ ለምሳሌ እንጀራ ለመብላት ስራ መስራት እንዳለብን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ስራው ግን በጥራት መሰራት አለበት፡፡ ስራ ማለት በአካል የሚታየው ውጤት ብቻ አይደለም፡፡ ስራውን ስንሰራ ሶስት አብረው የሚሄዱ ሃሳቦች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ስራውን ለመስራት የምንቀይሰው እቅዳዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሁለተኛው ስራውን ስንሰራ በስራው ሲደት ውስጥ የምንሰጠው ትኩረታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሶስተኛው ስራው ካለቀ በኋላ የሚሰጠን ውጤታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሶስተኛው ደረጃ ላይ የምናገኘው ርካታ ወይም ክለሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ባጭሩ አባባል የትኛውም የስራ ሂደትና ፍጻሜ ላይ፤ ሃሳብ ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡ ቀለም ለመቀባት እንኳን ቀለምና ቁሳቁስ ለምግዛት ማሳብ አለብን፡፡ ደረጃውን ጠብቆ እንዲያምር ተጠንቅቀን እያሰብን መቀባት አለብን፡፡ ስንጨርስ ደግሞ ውጤቱ ላይ እያሰብን እንኖርበታለን፡፡ ብዙ ነገሮች ቢያንስ ሶስት ደረጃ አያጣቸውም፡፡ ለምሳሌ ልክ እንደ መወለድ፣ መኖርና ህልፈት፡፡

ደጉ ሃገራት ጥቁር ህዝብ በስራ ሰነፍ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ እኔ ይኸን በቅርብ አውቀዋለሁ፡፡ ሆኖም ግን ከስራው ይልቅ አስተሳሰብ ይቀድማል ይመስለኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ማሰብም መስራት ነው፡፡ ለምሳሌ ያደጉ ሃገራት በስራና በሃገራቸው ላይ ቀልድ የለም፡፡ ሀገራቸውን ሀገሬ ይላሉ፡፡ ህዝባቸውን ህዝቤ ወይም ወገኔ ይላሉ፡፡ የሃገራቸውን ሃብት የኛ ይላሉ፡፡ ሃሳባቸው ውስጥ ቁርጥ ያለ አቋም አላቸው፡፡ እንዲሁ በድንገት አላደጉም፡፡ ያስባሉ፡፡ ይሰራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሆነ ግን ቀለም ለማስቀባት፣ ድንጋይ ለማንጠፍና፣ ሲሚንቶ ለመለሰን እንኳን ባለቤቱ ቆሞ መከታተል አለበት፡፡ ምክንያቱም ስራው ነካ ነካ ስለሚሆን መተማመና የሚሆን ዋስትና የለም፡፡ የስራ ባህላችን ገና አልዳበረም፡፡ በቀላሉ ማዳበር ግን እንችላለን፡፡

ከላይ እንደጠቀስሁት መስራት አቅቶን ሳይሆን ስራችን ላይ ጀግናዊ አስተሳሰብ ስለማይጨመርበት ነው፡፡ አንተ ደሞ ማጋነን ትወዳለህ አትበሉኝ! ጥሩ አላማ ላይ ማጋነን ቆንጆ ነው፡፡ ለምን ብትሉኝ ስራውን ስንሰራ ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ ይረዳናል፡፡ በተጨማሪ ሃሳባዊ ወኔ ውስጣዊ ስለሆነ የትም ብንሄድ ይከተለናል፡፡ የትኛውንም ስራ ብንሰራ ጥራት ያስታውሰናል፡፡ ስራችን ያኮራናል፡፡ ያስከብረናል፡፡ ተቀጥረን የምንሰራም ከሆነ አሰሪያችን ያምነናል፡፡ መከታተል ሳይሆን መጨረሻ ላይ ለማስረከብ መቆጣጠር ብቻ በቂ ይሆናል፡፡ ጥራት መፈለግ ቅንጦት አይደለም፡፡ በሰሪና ባሰሪ መሃከል እምነት ይጨምራል፡፡ ተመሳሳይ ጽሁፎች ይቀጥላሉ፡፡

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!