mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

ረጋ ማለትና ጊዜ መጠቀም

mejemer ethiopia hero

ሳባችን ላይ ረጋ ማለትና ጊዜ መጠቀም መጨረሻ ላይ ጥሩ ሽልማት አለው፡፡ ምናልባት የሚያኮራ ባይሆንም አስተሳሰቡ ነጥብና ምክንያት ካለው ግን የሚያሳፍር አይሆንም፡፡ ሁሉም ነገር ላይ ሁል ጊዜ አዋቂ መሆን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ቃላትና ተግባራችን ሁልጊዜ ፍጹም አይሆኑም፡፡ የሚያሳፍሩ መሆን ግን የለባቸውም፡፡ አቋማችን በቀጥታ ተቀባይነት ባያገኝም የሚናቅና የማይረባ መሆን የለበትም፡፡ ለመወደድ ብሎ ሰወች የሚፈልጉትን መናገር፤ በጣም ተራ ነገር ነው፡፡

አንድ ቀን፤ ከጊዜ በኋላ መጋለጡ አይቀርም፡፡ ለመግባባት በማሰብ ግን ሰወችን መጠጋት ለመከባበር ጥሩ መንገድ ይከፍታል፡፡ በዚህ አይነት አቀራረብ የሚገኝ መከባበር ለብዙ ጊዜ መቆየት ይችላል፡፡ መጨረሻ ላይም አያሳፍርም፡፡ አያስንቅም፡፡ ማፈርና መናቅ ማን የሚፈልግ አለ? እኔ እስከማውቀው ድረስ ማንም የለም! ለምሳሌ ነጋዴ የሚነግደው የሚያዋጣውን አይቶ ነው፡፡ ትምህርት ቤት የምንሄደው እውቀት ፍለጋ ነው፡፡ ስራ የምንሰረው እራሳችንን ለመርዳት ነው፡፡ እረፍት የምንወጣው ለምዝናናትና አእምሮአችንን ለማደስ ነው፡፡ ቤተሰብ የምንመሰርተው ትውልድ እንዲቀጥል ነው፡፡

መነገድ፣ ትምህርት ቤት መሄድ፣ ስራ ማግኘት፣ እረፍት መውጣት፣ ቤተሰብ መመስረት የመሳሰሉት የተለመዱ ናቸው፡፡ ህይወታችን የተሰተካከለ እንዲሆን በሁላችንም እይታ ተቀባይነት አላቸው፡፡ ሃሳባችን የተስተካከለ ሆኖ ተሰሚነት ለመግኘት ግን ቀላል አይደለም፡፡ በጣም ተፈታታኝ ነው፡፡ ምን አስቤ ብናገር ተሰሚነት አገኛለሁ? ምን አድርጌ ባሳይ ተቀባይነት አጋኛለሁ ብሎ መጠየቅ ስለሚፈልግ ቀላል አይደለም፡፡ እንደዚህ ብሎ እራሱን ለሚጠይቅ ሰው ግን ተቀባይነቱና ተሰሚነቱ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ተሰሚነትና ተቀባይነት በህይዎታችን ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫዎታሉ፡፡

ዚህም ነው መናገርና ማድረግን ከሁሉም በላይ መርጨ ያነሳኋቸው፡፡ ብዙ ሁነታዎች ላይ አብረው ይሄዳሉ፡፡ ይኸ እንዳለ ሆኖ ደግሞ ሰዎች ነንና ሁሉም ነገር ፍጹም አይሆንም፡፡ ስለዚህ ምናልባት ያልኩት ነገር ተሰሚነት ባያገኝም ነጥብ አለው፡፡ ያደረኩት ነገር ተቀባይነት ባይኖረውና ባያኮራኝም አላፍርበትም ብሎ ማሰብ የተሻለና የበለጠ እንዲናደርግ ያበረታታናል፡፡ ለምሳሌ አሁን እኔ ዛሬ የምናገረው የዛሬው ማንነቴ ነው፡፡ ወደፊትም ቢሆን መሰረታዊ ነገሩ ብዙ እንደማይቀየር ይሰማኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ነገ ወይም ከአመታት በኋላ፤ ተመልሼ ሳየው አሳፋሪ ሆኖ እንዲጠብቀኝ በጭራሽ አልፈልግም፡፡ የዚህ አይነት አስተሳሰብ እራሴን ለበጎ ነገር ለማዘጋጀትና ለማዘዝ ያነቃቃኛል፡፡ ባጭሩ አባባል በተቻለ መጠን እርሴን አርማለሁ፡፡ እራሴን እቆጣጠራለሁ ለማለት ነው፡፡ እራሴን ለማረምና ለመቆጣጠር የማደርገው ጥረትና የማሳየው ፍላጎት፤ መብቴን ይጋፋዋል ብዬ አላስብም፡፡

ይኸን ለማሳካት ደግሞ የመጀመሪያው ጥሩ እርምጃ፤ ረጋ ማለትና ጊዜ መጠቀም ጥሩ አማራጭ ይመስለኛል፡፡ በተልይ ከስራና ከትምህርት በኋላ ያለን ሃሳብና ጊዜ በትክክል ከተጠቀምንበት የበጎ አስተሳሰብ አምራች ፋብሪካ ያደርገናል፡፡ ገንዘብ አይከፈልበትም፡፡ እንዴት እንደሆነ በደንብ ላስረዳ፡፡ ለምሳሌ ስንበላ ማሰቢያ ጊዜ አለን፡፡ አጭርና እረዢም ጉዞ ስናደርግ ማሰቢያ ጊዜ አለን፡፡ ስፖርት ስንሰራ፣ ምግብ ስንሰራ፣ ስንዝናና ለማሰቢያ የሚሆን ትርፍ ጊዜ አለን፡፡ መጽሃፍ ማንበብ ቢሆንም በትርፍ ጊዜያችን የምናደርገው ነው፡፡ የተለየ ዝንባሌ ካለንም በትርፍ ጊዜያችን የሚደረግ ነው፡፡ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ገብተን ስንተጣጠብ ማሰቢያ ጊዜ አለን፡፡ ለእንቅልፍ ጋደም ከማለታችን በፊት ሃሳባችንን ለማሰባሰብ በቂ ጊዜ አለን፡፡ ጸሎት ስናደርግ ሃሳባችንን ለማረጋጋት በቂ ጊዜ አለን፡፡ ምሳሌዎቹ ብዙ ናቸው፡፡ አዕምሯችን በየትኛውም ቦታና ጊዜ ከኛው ጋር አብሮ ነው፡፡ የትም መሄድ ይችላል፡፡ አርቆ ማሰብ ይችላል፡፡

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!