mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

የምልክት አቅጣጫ

mejemer ethiopia amaharic sign direction

ንድ የሆነ ሰው ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ፤ ሰላም የምትፈልጉ በሙሉ፤ እስኪ እጃችሁን አውጡ ብሎ ድንገት ከጠየቀ ምን ይፈጠራል ይመስላችኋል? ሁሉም ሰው እጁን ላያወጣ ይችላል፡፡ ሁሉም ሰው ግን፤ ሰላም እንደሚፈልግ በውስጡ ይታወቀዋል፡፡ ከፍላጎት ግለት የተነሳ፤ እንደኔ አይነቱ ሁለቱንም እጆች የሚያወጣ ሰው አይጠፋም፡፡ ሁለት እጅ ማውጣ ምን ችግር አለው፡፡ ደግሞ ሰላም ተገኝቶ ነው! ሰውዬው እንደሆነ እግር አውጡ አላለም፡፡ ምግብ የምትፈልጉ ብሎ ቢጠይቅ፤ ተጨማሪ ምግብ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ሰው ምግብ አያንሰውም፡፡ ወደ አዳራሹ ሲመጣ በልቶ የመጣ ሰው አይጠፋም፡፡ ገንዘብ የምትፈልጉ ብሎ ከጠየቀ፤ ለትርፍ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ሰው ገንዘብ አያጣም፡፡ እኪሱ ውስጥ፤ በቂ ገንዘብ ያለው ሰው አይጠፋም፡፡ በሰላም ለመቆየት ግን፤ እርግጠኛ ነኝ ሁሉም ሰው ይፈልጋል፡፡ ዛሬም፤ አሁንም፤ ነገም፡፡ ወደኛ የሚመጡና ከኛ የሚወጡ ምልክቶችን አብረን እናያለን፡፡

ከዚህ በፊት እንደጠቀስኩት፤ በህይወታችን ውስጥ፤ ሰው ሰራሽ በሆኑ ምልክቶች ተከበናል፡፡ ለነዚህ ሰው ሰራሽ ምልክቶች፤ የምንሰጠው መፍትሄ ግን፤ እንደ አስተሳሰባችን፤ እንደ ባህላችን፤ እንደ አስተዳደጋችን ይለያያል፡፡ አንድ አይነት መሆንና ማሰብ ስለማይቻል፤ የመፍትሄው አይነትና ብዛት የተለያየ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ግን ልብ ብላችሁ ከሆነ፤ መጨረሻ ላይ የምንፈልገው ውጤት ይመሳሰላል፡፡ ሰፍ ያሉለት ነገር በቀላሉ አይገኝም የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ትልቁ ፈተና ያለው ግን ሰላም እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ማወቁ ላይ ነው፡፡ ብዙ እርቀን ሳንሄድ ሰላም ከግለሰብ ምልክት ላይ ይጀምራል፡፡ ዛሬ ሁለት አይነት ምልክቶችን አብረን እናያለን፡፡

ሁለት አይነት ሰው ሰራሽ ምልክቶች አሉ ብየ አስባለሁ፡፡ ምልክት ማየትና ምልክት ማሳየት ናቸው፡፡ ምልክት ማየት ማለት፤ የኛ ያልሆነውን ምልክት ማየት መቻል ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ይኸን ምልክት ማየት እንጂ መቆጣጠር አንችልም፡፡ የምልክቱ ባለቤት እኛ አይደለንም፡፡ ምልክት ማሳየት ደግሞ፤ ከኛ ከውስጣችን የሚወጣ፤ ከውስጣችን የሚፈልቅና ወደ ውጭ የምናሳየው ምልክት ነው፡፡ የምልክቱ ባለቤት እኛው እራሳችን ነን፡፡ ለሌላ አሳልፈን የምናሳየው ምልክት ነው፡፡ አሁን ሁለቱንም ምልክቶች ለማብራራት ልሞክር፡፡

ምልክት ማሳያ መነሻው፤ ባየነው፣ በሰማነውና ተካፋይ በሆንበት ጉዳይ ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ የታየውን ነገር፤ ልንወደው ወይም ልንጠላው እንችላለን፡፡ የሰማነው ነገር ሊያስደስተን ወይም ሊያበሳጨን ይችላል፡፡ ተካፋይ የሆንበት ጉዳይ ፍሬ ያለው ወይም ፍሬ-ቢስ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከማየት፣ ከመስማትና ተካፋይ ከመሆን ሙሉ በሙሉ መራቅ አይቻልም፡፡ ይኸ የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ፤ በማየት፣ በመስማትና ተካፋይ በመሆን፤ ያገኘነውን ልምድ የምናሳይበት መንገድ ነው፡፡ ይኸ ማለት፤ ውጫዊ ምልክት እንደምናየው ሁሉ፤ እኛም ከውስጣችን ወደ ውጭ የምናሳየው ምልክት አለን፡፡ ለምሳሌ ባየናውና በሰማነው ነገር ላይ፤ ማመን ወይም አለማመን ሊሆን ይችላል፡፡

ምልክት ስናሳይ ግን፤ ከወጣ በኋላ ምን አይነት ምልክት ሊሆን እንደሚችል፤ ቀደም ብሎ ማሰብ መጥፎ ምልክት እንዳይሆንብን ያስታውሰናል፡፡ ለምሳሌ ካፋችን የሚወጡ ቃላት፣ የምንጽፈው ጽሁፍ፣ የምናሳየው ፊት፣ የምንወስደው ሃላፊነት፣ የሃሳባችን አገላለጽ፤ የአንድን ሰው ማንነትና ሰብዕና ማሳያ ምልክቶች ናቸው፡፡ ጥሩ ምልክት ማሳየት የማይችል ሰው፤ በሌላ ሰው እይታ ማንነቱ ላይ ጥሩ ስም የለውም፡፡

ምሳሌ እከሌ እኮ ነገረኛ ነው፣ የሚጽፈው አያግባባም፣ ፊቱ ጋባዥ አይደለም፣ ሃላፊነት አይሰማውም፣ ተሳዳቢ ነው፣ አቀራረቡ ይደብራል ይባላል፡፡ ከፍትፍቱ ፊቱ የሚባለው ለዚህ አይደለ? እንዲህ የተባለው ለፍትፍት ብቻ አይደለም፡፡ ስለምግብ ብቻ ያሰብኩ እንዳይመስላችሁ ግን አደራ! ጥሩ ምልክት የሚያሳይ ሰው ግን፤ ምን ይባላል መሰላችሁ፡፡ እከሌ ደግ ነው፣ የሚጽፈው ያግባባል፣ ፊቱ ዘና ያለ ነው፣ አቀራረቡ፤ አቤት ደስ ሲል! እራሱን የቻለ ነው፡፡ አስተሳሰቡ ደግ እንጅ ሞኝ አይደለም፡፡ ሃላፊነት ይወስዳል፡፡ መርዳትና መማር ይወዳል፡፡ በመስራትና በማሳየት ያምናል፡፡ ጥሩ ምልክት የሚያሳይ ሰው አብዣኛው ማንነቱ ከጥሩ ስም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ልብ ማለትና ትኩረት መስጠት፤ ከምልክት ማንበብና ማየት ጋር ይመሳሰላል፡፡ አስታውሱ! ሁለት አይነት ሰው-ሰራሽ ምልክቶች ናቸው፡፡ እንደጠቀስኩት ወደኛ የሚመጡና ከኛ የሚወጡ ምልክቶች፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ፤ የምልክት ጉዳትና ጥቅም ምን እንደሆነ ለማቅረብ እዘጋጃለሁ፡፡ ይከታተሉ፡፡

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!