mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

ኮምፕዩተር በቀላሉ እንዳይጠቃ ጥንቃቄ!

mejemer computer introduction

መጀመሪያ ሁኔታውን ግልጽ ለማድረግ ማንኛውም ኢንተርኔት ጋር የተገናኘ ኮምፕዩተር ለጥቃት የተጋለጠ ነው፡፡ ይህ ጥቃት ለምሳሌ የተጠቃሚውን የግል መረጃ፣ የተለያዩ ሰነዶችና ከንብረት ጋር የተያያዙ መረጃወችን ለመስረቅ ነው፡፡ ሌላው ጥቃት ደግሞ በፖለቲካ ምክንያትም ሆነ ወንጀለኞችን ለመከታተል የሚደረግ የስለለላ ጥቃት ነው፡፡ በድርጅቶችና በሃገሮች መከከል ደግሞ የተለያየ ቴክኖሎጂና መረጃ ለማግኘት አንዱ ከሌላው ይሰልላል ወይም ይሰርቃል፡፡

የተጠቃሚው ኮምፕዩተር እንዳይሰራ ለማድረግና መረጃወቹንም ለማበላሸት ተባይ እየሰሩ የሚያሰራጩም አሉ፡፡ እኛ በአካል ስለማናየው ነው እንጂ ከፍተኛ የሳይበር ጦርነት አለ፡፡ ለዚህ አላማ፣ ለመከላከልና ለማጥቃትም ጭምር ብዙ ገንዘብና የሰው ሃይል ይውላል፡፡ ዝም ብሎ ግለሰቦችን መሰለል ጥቅም ስለሌለው ብዙው ጥቃትና ስለላ የሚደረገው በድርጅቶችና በሃገሮች መካከል ነው፡፡

ነገር ግን ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ ያለ አምባገነን ሰርአት ያላቸው ሃገሮች ግለሰቦችንም ይሰልላሉ፡፡ አሁን እኔ በድርጅቶችና በሃገሮች መካከል የሚደረገው ስለላ የረቀቀ ስለሆነ አላውቅም፡፡ ግን አንድ ግለሰብ ኮምፕዩተሩ በቀላሉ እንዳይጠቃበት ለመርዳትና ፍንጭ ለማሳየት ነው፡፡ የግል ኮምፕዩተርን ከጥቃት ለመቀነስ ልክ የግል ቤትን መስኮትና በራፍ መቆለፍ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ወደ ከተማም ሲደርሱ መኪናን ፓርክ ካደረጉ በኋላ ሞተሩን አጥፍቶ መከላከያ አላርሙን ቀስቅሶና በራፎቹን ቆልፎ ወደ ሱቅ መሄድ ጋር ይመሳሰላል፡፡ በግልጽ እንደሚታወቀው ቤትን ካልቆለፉ እቃ ይዘረፋል፡፡ መኪናም ካልቆለፉ መኪና ውስጥ ያለው እቃ ይሰረቃል፡፡ መኪናዋ እራሷም ልትወሰድ ትችላለች፡፡ የቤቱም ሆነ የመኪናዋ ባለቤት በተቻለው ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ አልበት፡፡ ሁኔታው ተጋኖ ለምሳሌ ሌባው የተቆለፈውን ቤት በመጥረቢያ ፈልጦ ከገባ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡

ና ሲጀመር የሚያውቀውና መዝረፍ ያሰበው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይም ሌባው መኪናዋን በክሬን አንስቶ እንደተቆለፈች በጭነት መኪና ይዟት ጥርግ ቢል ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ባለቤቱ በቀላሉ እንዳይጠቃ የመጀመሪያውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የማያውቁት ሰው በራፍ ቆርቁሮ መግባት ቢፈልግ ሳናጣራ ዝም ብለን ቤት ለንግዳ ብለን ቤቱን አናስረክብም፡፡ ይህን የሚያደርግ ሰው ካለ በቀላሉ ሊጠቃ የሚችል ቂል ሰው መሆን አለበት፡፡ መኪናዋንም በተመለከተ ለምሳሌ ባለቤቱ መኪናዋን እያሽከረከረ እንዳለ ድንገት አንዱ ለመፈናጠጥ ቢጠይቅ የማያውቁትን ሰው ማፈናጠጥ ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል፡፡

የኮምፕዩተር ደህንነት ለመጠበቅ የቤትና የመኪናው ምሳሌ ጋር ይመሳሰላል፡፡ የሚለያቸው ነገር ቢኖር የቤትና የመኪና ጥቃት አካላዊ ነው፡፡ የኮምፕዩተር ጥቃት ግን ስውር ነው፡፡ ይኸን ስውር የሆነ ኮምፕዩተር ጥቃት ለመከላከል ደግሞ እራሱን የቻለ ቀላል የሆነ የመከላከያ እርምጃ አለው፡፡ ይህ መከላከያ እርምጃ ግን እንደ ሽንኩርት ልጫ የተደራረበ ስለሆነ የሚያሰለች ሊሆን ይችላል፡፡ በደረጃና በሽፋን የተከፋፈለ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ሰወች ኮምፕዩተራቸው የሚጠቃው ባለማወቅና በችልተኝነት ነው፡፡ ዋናው የሚያጋልጣቸው ምክንያት ግን የኮምፕዩተር አጠቃቀም ባህሪያቸው ነው፡፡ ይህ እንዴት እንደሆነ የሚቀጥለው ክፍል ላይ አቀርባለሁ፡፡ የመጨረሻው ክፍል ላይ ደግሞ በቀላሉ ጥቃትን እንዴት መቀነስ እንደሚቻል በዝርዝር አቀርባለሁ፡፡

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!