mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

የስራ ቦታ ስነምግባር

mejemer ethics and the rules at work place

መጨረሻው ክፍል ላይ ደርሰናል፡፡ ካለፉት ሰባት ተከታታይ የስራ አፈላለግ ስልት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ተፈላጊው ስራ ከተገኘ በኋላ ስራ ቦታ ላይ የተጻፉ እና ያልተጻፉ ህጎችን አብረን እናያለን፡፡ ህጎቹ እንደ ሃገሩና ስራው አይነት ይለያያሉ፡፡ በቀላሉ አባባል ያገኙትን ስራ እንዴት ይዞ ማቆየት እንደሚቻል ለመግለጽ ነው፡፡

ልምምድና ማስታወሻ

አዲስ ስራ ላይ መጀመር ለማንም ሰው ቢሆን በጣም ደስ ይላል፡፡ ነገር ግን ስለ መስሪያ ቤቱ ባህልና የሰራተኞቹ አቀራረብ ወዲያውኑ በትክክል የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ግን የመጀመሪያ ቀን ላይ ከርስዎ በፊት የነበሩ ሰራተኞች ጋር ይተዋወቃሉ፡፡ የስራዎ ድርሻ የት እና ምን እንደሆነ ማወቂያ ጊዜ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ቀናትና ወራት ውስጥ የተወሰነ ልምምድ ሊሰጥዎት ይችላል፡፡ ልምምድ በሚሰጥ ጊዜ ማስታወሻ መያዝ ለወደፊቱ ይጠቅማል፡፡ ሌላ ጊዜ የረሱት ነግር ቢኖር ሰው ከመጠየቅ ማስታወሻ ማየት ይሻላል፡፡ ማስታወሻ መያዝን የመሰለ ምርጥ ነገር የለም፡፡ እናስታውሳለን ብለን ሃሳባችን ውስጥ በእርግጠኝነት የያዝነው ነገር ከቀናት በኋላ ይረሳል፡፡ በህይዎታችን ውስጥ ሌላ ነገርም ላይ ቢሆን ማስታውሻ መያዝ ትዝታ ይቀሰቅሳል፡፡ ማስታወሻ የማስታወስና የመተንተን አቅም ከፍ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ነው ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም የሚባለው፡፡ ሃሃ፡፡ ማስተወሻ ሲይዙ ግን የግድ በዝርዝር መሆን የለበትም፡፡

ለምሳሌ ከድሬደዋ ወደ አ.አ. ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና እየነዱ መሄድ ከፈለጉ አቅጣጫው እና ለመድረስ ስንት ጊዜ እንደሚወስድ ማወቅና ማስታወስ በቂ ነው፡፡ መንገድ ላይ ማረፍ ካስፈለገና ቤንዚን መሙላት ካስፈለገ፤ ጉዞው ላይ ተስማሚ ጊዜና ቦታ ሲገኝ መጠቀም ይቻላል፡፡ ሁሉንም ነገር መዝግቦ መያዝ አይመችም፡፡ ስራ ቦታ ላይ ቢሆንም ማስዎሻ አጭር መሆን አለበት፡፡ ተመልሰው ሲያዩት ግን በዝርዝር ትዝታ የሚቆሰቁስ መሆን አለበት፡፡ ጭንቅላታችንም ከልቡ የሚሰራውና የቆየ ነገር አስታውሶ የሚዳብረው በዚህ አይነት ዘዴ ይመስለኛል፡፡ ልምምዱ ስለ ስራው ሙያ ብቻ ሳይሆን ስለ መስሪያ ቤቱም የበለጠ እንዲያውቁ በደንብ መከታተል አለብዎት፡፡ ለወደፊቱ የርስዎ አቀራረብ ምን መምሰል እንዳለበት ፍንጭ ይሰጥዎታል፡፡ ዋናው ነግር ግን ልምምዱ በስራ እና ባቀራረብ ላይ ምን አይነት ማሻሻያ ማድረግ እንደሚቻል አቅጣጫ ያሳያል፡፡

ስራየ እንጀራየ ነው፤ ታማኝነት!!

ንድ ሰራተኛ ስራየ እንጀራየ ነው ብሎ ሊሰማው ይገባል፡፡ የዚህ አይነት ስሜት ስራ ቦታ ላይ ታማኝ ያደርጋል፡፡ ባለቤትነት እንዲሰማን ያደርጋል፡፡ ስራ ቦታ ላይ ጥሩ መንፈስና ስሜት ይፈጥራል፡፡ የቤተኝነት ስሜት ከአካፋ እና ዶማ እስከ ኮምፕዩተርና ቤተ-ሙከራ መሳሪያወች ወዘተ ድረስ የእንጀራየ ምንጭ ናቸው ብሎ ለማሰብ ይገፋፋል፡፡ እንደ ግል ንብረታችን እንግብካቤ ለማድረግ እንብረታታለን፡፡ ለመስሪያ ቤት ሚስጥርና መረጃም ታማኝ መሆን አንዱ የስራው አካል ነው፡፡ ከስራ ቦታ ውጭ ቢሆንም እምነት ዋና ቁልፍ ነው፡፡ ለምሳሌ ለጓደኛ እና ለወዳጅ፤ ለቤተሰብና ለሃገር ታማኝ መሆን ትርፍ አለው፡፡ ለዚህም ነው ለጓደኛና ለወዳጅ ታማኝ ያልሆነ ከሃዲ የሚባለው፡፡ ለቤተሰብ የማይታመን ወስላታ የሚባለው፡፡ ለሃገርሩ ታማኝ ያልሆነ ባንዳ የሚባለው፡፡ በስራው ታማኝና ታታሪ ያልሆነ እምነት አያገኝም፡፡

እንደ አጋጣሚ ሆኖ ስራውን ካልወደዱት የባለቤትነት ስሜቱ ግን መጥፋት የለበትም፡፡ ምን እንዲሆነ ምክንያቱን ፈልጎ ማግኘት ይሻላል፡፡ ለምሳሌ የስራ ጭነት ከሆነ አስፈላጊውን ስራ ማስቀደም ሊሆን ይችላል፡፡ ስራው ትንሽ ከበድ ካለ በትርፍ ጊዜ ቢሆንም የሚያቀል ነግር ፈልጎ ማጥናት ሊሆን ይችላል፡፡ ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ካስፈለገ በመስሪያ ቤቱ በኩል ወይም በግል ልምምድ ወይም ኮርስ መውሰድ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሌሎች ሰራተኞች ጋር ለመግባባት ማህበራዊ ኑሮው ያነሰ ከሆነ የራስዎን አቀራረብ ማስተካከል ሊሆን ይችላል፡፡

እኔ እኔ ማለት ይጎዳል ወይስ ይጠቅማል?

በየጊዜው እኔ የምትለዋን ቃል ካላበዙ፣ ስራዎ ላይ የበለጠ ካተኮሩ፣ ፈገግ ካሉ፣ ሰላም ሲሉ ድምጽዎ የጠራና የጎላ ዜማ ካለው፣ ፊትዎ ዘና ካለ የማህበራዊ ኑሮው በቀላሉ ይሻሻላል ብየ አስባለሁ፡፡ ሰርተው ያስገኙትን ውጤት ለማሳወቅ እድል ሲያጋጥምዎት ያላስፈላጊ እኔ የምትለዋን ቃል ካላበዙ ብዙ ያስኬዳል፡፡ ለምሳሌ አሁን ጨርሻለሁ ከማለት ይልቅ አሁን ዝግጁ ነው ማለት ይሻላል፡፡ ወይም አሁን አልቋል ማለት ብቻውን የበለጠ ተቀባይነት አለው፡፡ የስራ ባልደረቦችዎ ዋጋ ይሰጡታል፡፡

አንዳንድ ሰወች እኔ ማለት ስለሚያበዙ ባጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሰው ስለነሱ ስሜት የለውም፡፡ የርስዎ ልፋት እና ውጤት መሆኑን ለማሳየት ሁል ጊዜ እኔ ማለት ሙሉ በሙሉ ማረጋገጫ አይደለም፡፡ አስፈላጊ በሚሆን ጊዜ አባባሉን አሳምረው እኔ ማለት ይችላሉ፡፡ አባባሉና አቀራረቡ ላይ ነው እንጂ ማንኛውም ነገር ተቀባይነት አለው በሚባለው መርህ ካመኑበት፡፡

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!