mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

የስራ ማመልከቻ አጻጻፍ፣ ሂደትና ክትትል

mejemer get the job follow ups

ራ ማመልከቻ የአመልካቹን ማንነት የሚገልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ስራ ማመልካቻ የችሎታና የማንነት መገለጫ መጽሃፍ ነው፡፡ ጥሩ ስራ ለማግኘት አቋራጭ መንገድ የለም! ክትትልና ልፋት ይፈልጋል፡፡ ትኩረት ይጠይቃል፡፡ ኮተት ሳይበዛበት አጠር ብሎ ግልፅና ለመረዳት ቀላል መሆን አለበት፡፡ ቀጣሪዎች ብዙ ማመልከቻዎች ይደርሷቸዋል፡፡ እጥር ምጥን ያሉና መስመር ያልሳቱ ማመልከቻወች ይመርጣሉ፡፡

ማመልከቻ ሲፅፉ ቀን፣ የእርስዎ ሙሉ ስምና አድራሻ ይቀድማል፡፡ ከዚያም የስራው አይነት ከነ አርእስቱ ጎላ ብሎ በአርእስት መልክ ገባ ብሎ ይሰፍራል፡፡ ወደ ዝርዝር ከመግባትዎ በፊት ስራውን በተመለከተ መቼና ከማን ጋር በስልክ ጥሩ ውይይት እንደነበረዎት ቢጠቅሱ ይታዎሳሉ፡፡ ከዚያም ይኸን ስራ ለምንና እንዴት እንደፈለጉት ባጭሩና በዝርዝር ያቀርባሉ፡፡ የትምህርት ጊዜ፣ የስራ ልምድ፣ በትርፍ ጊዜ የሚደረጉ የተለያዩ ዝንባሌዎች፣ ወዘተ እራሱን በቻለ ገጽ ላይ እጥር ምጥን ብሎ መቅረብ አለበት፡፡

በተለይ አመልካቹ ባሁኑ ጊዜ ምን እንደሚያደርግና ህይወቱ ምን እንደሚመስል በገንቢ መልክና ባጭሩ ቢያቀርብ ማመልከቻውን ሁለገብ ያደርገዋል፡፡ አመልካቹ በራሱ አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን የራሱን ሁኔታዎችና ልዮ ችሎታዎች ቢጠቅስ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ በመጨረሻም አመልካቹን የሚያውቁና ፈቃደኝነታቸው የታወቀ የሁለት ወይም ሶስት ተጠሪ ግለሰቦች ስም ከነሙያቸው ከማመልከጫው ጋር ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ የተጠሪዎቹ ስም ለቃለ ምልልስ ሲቀርቡም ማሳወቅ ይችላሉ፡፡ ይኸን እንደ ምርጫዎና እንደ ስራው ማስታወቂያ አይነትና ፍላጎት ይለያያል፡፡ ተጠሪዎቹም ድንገት ተደውሎላቸው እንዳይደናገሩ ጉዳዩን በቅድሚያ ይንገሯቸው፤ ያስታውሷቸው፡፡

ራመልከቻው ከተላከ ከሶስት እስከ አምስት ቀናት በኋላ ከዚህ በፊት ያነጋገሩትን ሰው እንደገና ደውለው ማነጋገር ይችላሉ፡፡ ስልኩን እራሱ ሰውዬው ካነሳው/ችው በስም “ ሰላም እከሌ” ብሎ ንግግር መጀመር ነው፡፡ ለምሳሌ “በዚህ ቀን ላይ ስለዚህ ስራ ተነጋግረን ነበር፡፡ ማመልከቻ ልኬአለሁ፡፡ ስለ ማመልከቻው ምን ይመስልዎታል? ሌላ ተጨማሪ ነገር የምትፈልጉት ካለ እልካለሁ፡፡” ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ማመልከቻው እስከዛሬ ድረስ ያልተነበበ ከሆነ አሁን ስለደወሉ ማመልከቻው ከተቀመጠበት ተነስቶና ተመዞ ወጥቶ ሊነበብ ይችላል።

ዋናው ቁም ነገር ግን አርስዎ አሁን እራስዎን እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ አስተዋወቁ፡፡ ማመልከቻውን በደንብ እየተከታተሉ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያነጋገሩትን ሰው ስምና ቀኑን አስታወሱ፡፡ ስራው ለማግኘት ያለዎትን ፍላጎት እንደገና አሳዩ፡፡ ማመልካቻው ከንብብሩ ላይ ተነስቶ ወይም ተመዞ ሊታይልዎት ይችላል፡፡ ቀጣሪውም አርስዎን በቀላሉ ያስታውሰዎታል፡፡

የስልክ ንግግሩ በሚካሄድበት ጊዜ እርስዎ እንደ ስራ ለማኝ ወይም ተስፋ ቢስ አይነት ሆነው በፍጹም መታየት የለብዎትም፡፡ ባነጋገር ሁኔታና በድምፅ ቃና በራስዎ የሚተማመኑ መሆንዎን ማሳወቅ መቻል አለብዎት፡፡ ይህ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በስልክም ቢሆን ይታወቃል፡፡ ላልተጠበቁ ጥያቄዎችና መልሶች በስልክም ቢሆን ዝግጁ መሆንና በተቻለ መጠን ምክንያታዊ የሆነ ጥያቄ ማቅረብና መልስ መስጠት ከቀጣሪው ነጥብ ያሰጣል፡፡ መጨረሻ ላይ አመስግነው ለቃለ ምልልስ እንድምጠራ ተስፋ አደርጋለሁ ሳይሆን ለቃለ ምልልስ እንደምጠራ እጠብቃለሁ ብለው በጨዋነት የስልኩን ንግግር መጨረስ ነው፡፡ ዘንድሮ እኮ አጉል ደፋርና ፈጣጣ ሆንኩኝ ብለው አይስጉ። እንደ ሞኝ ሆነው ካልቀረቡ በስተቀር እስካሁን ድረስ ማመልከውን በትክክል እየተከታተሉ ነው፡፡ ልምድም እየወሰዱ ነው፡፡

ዋናው ነገር ወሬ ሳያበዙ ባጭሩ መጠየቅ፣ መልስ መስጠትና በጊዜው ውይይቱን መጨረስ ነው። ብዙ ካወሩ ለመሳሳት እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ደግሞ ከማያውቁት ሰው ጋር ብዙ ማውራት አያስፈልግም፡፡

በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ለቃለ ምልልስ ካልተጠሩ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ሌላ ስራ ለማግኘት እንደገና መጀመር ብቻ ነው፡፡ ማዘንና መጨናነቅ ሳይሆን ልምድ ይውሰዱበት፡፡ ለቃለ ምልልስ ከተጠሩ ደግሞ እሰየው ነው፡፡ አንድ እርምጃ ወደፊት፡፡ በሚቀጥለው ክፍል 3 ላይ ለቃለ ምልልሱ እንዴት መዘጋጀት እንዳለበዎት አብረን እናያለን፡፡

ለማስታወስ ያህል የመጀመሪያው የስራ አፈላለግ ስልት ላይ በዝርዝር የሚከተሉትን ነጥቦች አይተናል፤

ለስራ ፍለጋ ቅድሚያ ዝግጅት፣
ክፍት የስራ ቦታዎች ምን ላይና እንዴት እንደሚወጡ፣
ማመልካቻ ከመጻፉ በፊት ስለሚደርጉ ቅድመ ዝግጂቶች፣
የማመልከቻ አጻጻፍና ክትትሉን አይተናል፡፡
ክፍል 4 ላይ ይቀጥላል!

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!