mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

የአስተሳሰብ ሽፍታ

mejemer ethiopia amharik thinking rebel

ለፈው ጊዜ መርህ ማለት ምን እንደሆነ ጽፌ ነበር። ቀጥሎ ደግሞ መርህ ከየት ማዳበር እንደሚቻል ለማስረዳት ሞክሬ ነበር። ዛሬ ደግሞ በቂ መርህ የሌለው ዜጋ የህይወቱ ደረጃ ምን እንደሚመስል ላስረዳ። እንደሚታወቀው መርህ ማለት አንድ ሰው በህይወቱ ውስጥ መጠቀም የሚፈልገው ሚዛናዊ አስተሳሰብና ግብ ነው። ጥሩ መርህ ካለወት ጽሁፉን ያንብቡት እንጂ ሁሉም ሰው መርህ ያንሰዋል ማለቴ አይደለም።

የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት፤ ለመሰረታዊ ኑሮ ምግብ፣ መጠጥ፣ ልብስና መጠለያ ያስፈልገናል። ወጪ ለመሸፈን ገንዘብ ያስፈልገናል። ገንዘብ ለማግኘት ስራ ያስፈልገናል። ስራውን ለማግኘት ትምህርት ያስፈልገናል። ለመተንፈስ አየር መሳብ አለብን። መሰረታዊ ፍላጎታችን እንደ ሰንሰለት የተያያዘ ነው። ነገር ግን የሰው ልጅ በመሰረታዊ ፍላጎት ብቻ አይኖርም። መርህ የሚባል የአዕምሮ ምግብ ያስፈልገዋል።

የአዕምሮ ምግብ፤ መርህ ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም መርህ በሚኖረን ጊዜ እጃችን ትክክለኛ ነገር ይነካል። ልባችን ተገቢ ርህራሄ ያሳያል። አፋችን የሚያግባባ ቃላት ያወጣል። ለምሳሌ በቃል መገኘት፣ ባህሪ ማሳመር፣ ማመዛዘን መቻል፣ መከባበር፣ አዲስ ነገር መማር፣ ስህተት መቀነስ የአእምሮ ምግብ ናቸው። ሰውን ከእንሰሳ የሚለየው ዋነኛ ምክንያት መርህ ነው።

ምሳሌዎች፤ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ ምግብ የለም። አንዱ የመርህ ማነስ መገለጫ ዲያስፖራ ከኢትዮጵያ የሚመጣ ምግብ መብላት ማቆም ባለመቻሉ ነው። የባህል ምግብ በመሆኑ ሳይሆን ብዙወቻችን በችጋር ያደግን ስለሆነ ነው። ኢትዮጵያዊ ተካፍሎ ይበላል የሚባለው ችጋር ስላለ ነው እንጂ ደግ ነገር ሆኖ አይደለም። እየተካፈልን ሳይሆን እየተሻመን ያደግን ይመስላል። በተለይ ዲያስፖራው እንደ ነገሩ ጠርጎ ወይም የቢሮ ስራ ሰርቶ ገንዘብ ካገኘ እና የፈለገውን መግዛት ከቻለ ሃገርቤት ያለውን ችግር የረሳው ይመስላል። ምግብ ግን ዛሬ በልተነው ነገ በመቀመጫችን ቱቦ ይወጣል። ተደብቀን፣ መጸዳጃ ቤት ዘግተን፣ ጠርገንና ታጥበን እንወጣለን። ምግብ ለመሰረታዊ ፍላጎታችን አስፈላጊ ቢሆንም ከቆየ በኋላ ሲወጣ የዚህን ያህል አስቀያሚ ነው። እንዲህ ስለሆነ ነው መሸሸጊያ ጉድጓድ የሚቆፈርለት።

ሰው ልጅ ግን ለስጋው ብቻ ሳይሆን ለነፍሱ አብልጦ መኖር ነበረበት። እንደ ሚባለው እውነተኛ አማኝ ብንሆን ኖሮ ነብሳችን ህያው መሆን ነበረባት። በችጋር ማደግ ግን እራስ ወዳድ ያደርጋል። ወፍ እንኳን ምግብ ከየትም ፈልጋ ለልጆቿ በአፋቸው ታቀብላለች። አምበሳ ለልጆቿ ምግብ እንዴት እንደሚያድኑ ታሳያለች። አንዳንድ የቤት እንሰሳዎች ሳር አሽተው የሚመርጡ አሉ። እኔ በልጅነቴ እረኛ ነብርኩና በአይኔ አይቻለሁ። የኛ ህዝብ ግን ሳይቸግረው ምግብ ለመቀማት ምክንያቱ ብዙ ነው። ከቤተሰብ ካላየ፣ ከት/ቤት ካልተማረና በራሱ ካልደረሰበት ሞራል የሚባል የአዕምሮ ምግብ የጠፋ ይመስላል። እምነት ቤት መመላልስ፣ በአፍ ብቻ ስለ ፍቅርና አንድነት ማውራት ወሬ ብቻ ነው። እነዚህን ነጥቦች ያነሳሁት ለመጠየቅ እንጂ ማንንም ለማበሳጨት አይደለም።

ተጨማሪ ምሳሌዎች፤ በቀጠሮ ዘግይቶ የት እንዳለ ሳይሆን እየመጣሁ ነው የሚል ህብረተሰብ አለን። ግልጽ መሆን ገና አልተለመደም። ሰአት አሳልፎ ስብሰባ መጀመርና መጨረስ በህበረተሰባችን ውስጥ ይታያል። ትክክል መሆን ገና አልተለመደም። መሪ ከላይ መጣ ብሎ የሚቀበል ህብረተሰብ አለን። የባሪያ ስነ-ልቦና እስከ አሁን ድረስ አልቀረም። የሆነ ነገር ለመደገፍ፣ ለመቃዋምና ለማጨብጨብ የሚቸኩል ህብረተሰብ አለን። እውነት ወይም ውሸት መሆኑን አጣርቱ ለማሰብ ያለን ልምድ እና አቅም አነስተኛ ስለሆነ ነው። ለሰው ልጅ ህይወት ሳይሆን ለሃይማኖት የሚጮህ ህብረተሰብ አለን። ነገር ግን ሰው ከሌለ ሃይማኖት የለም። ቡና ለመጠጣት ብዙ ሰዓት የሚያቃጥል ህብረተሰብ አለን። በትርፍ ጊዜው በእውቀት የሚያዝናናው ምርጫ አላስቀመጠም። ያልተፈቀደ ጥበብና ሙዚቃ ቅዳልኝ የሚል ህብረተሰብ አለን። ጥበበኞች የለፋበትን ስራ በነጻ ለመጠቀም ይፈልጋል። ሰበር ዜና አርዕስቱን ትቶ ሌላ ትረካ ውስጥ የሚገባ ህብረተሰብ አለን። ማታለል የተለመደ ነው።

የአስተሳሰብ ሽፍታ፤ ብዙ ከመርህ ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉን። አንዳንዶቹን ብቻ ነው በምሳሌ የጠቀስኩት። የሰው ልጅ ከትንሽ ነገር ጀምሮ ትክክል መሆን ካልተለማመደ ትልቅ ነገር መገንባት አይችልም። አሁን ያለንበት የህይወት መለኪያ ደርጃ እንዲህ የወረደው የሆነ ነገር አጥፍተን መሆን አለበት። እንዴት እናውቀዋለን? የሰው ልጅ እንደገና ተጠፍጥፎ አይሰራም። እራሱን ለመጠየቅ ግን መጀመር ይችላል። እራስን መጠየቅ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። የሚጠይቅ አንጀት ካለን። ለምሳሌ እኔ የችግር አካል ነኝ ወይስ መፍትሄ እፈልጋለሁ ብሎ መጠየቅ አንድ ጥሩ አማራጭ ነው። ጣት ከመቀሰር እና ባዶ ወሬ እያወሩ ከማለም ይሻላል። ምናልባት ይኸ ጽሁፍ ላይወደድ ይችላል። አላማው ለመወደድ ወይም ለመጠላት አይደለም። ጥያቄ ለመጠየቅ ነው።

ለምሳሌ ፈገግና ኮስተር ካሉ ጥያቄው ገብቶዎታል። ከተበሳጩ ጥያቄው በቀጥታ ይመለከተወታል ማለት ነው። ሁሉም ነገራችን ግን መፍትሄ ይፈልጋል።
1) አስተዳደግዎን ይመርምሩት። እንዴት ነበር?
2ኛ) የተማሩበትን ት/ቤት ያስታውሱት። ምን አስታወሰዎት?
3ኛ) አሁን የሚኖሩበትን ህይወት ያስተውሉት። ምን ይመስላል? ለአዕምሮዎ ምን አይነት ምግብ አለዎት?

ራስን መጠየቅ ይኸን ይመስላል። በአስተሳሰብ ሽፍታ ይሁኑ። ከጀሌ አስተሳሰብ ይላቀቁ። ከሳጥኑ ውጭ ማየት ይለማመዱ። ያኔ በተግባር ሰው መሆንዎን ያውቁታል። ከፈጣሪ አምላክዎ ጋር የተሻለ ቅርበት ይፈጥራሉ። እሰይ የኔ ልጅ ብሎ ይኩራብዎት። ከራሴ ጀምሮ ማንም ደንቆሮ ትምትርት ቤት ሄዶ የቀለም ትምህርት መማር ይችላል። የሰው ልጅ መለኪያው ድግሪ ሳይሆን በህይወቱ ውስጥ የሚኖርበት መርህ ሲኖረው ነው። እኔም የጻፍኩት ስህተት ሊኖረው ይችላል። ለመማር ግን ዝግጁ ነኝ።
ሰላም!

ከታች አስተያየት ወይም ኮከብ ለመስጠት ያስታውሱ!

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!