አፍራሽ አስተሳሰብ እንዲህ ይመስላል፡፡ ሰው ተጠቀመብኝ፡፡ ተበድያለሁ፡፡ ማንንም አላምንም፡፡ እጠራጠራለሁ፡፡ አልችልም፡፡ ዛሬ በቀኝ ጎኔ አልተነሳሁም፡፡ ዝናብ ስለሚጥል ተደበርሁ፡፡ የፈለገ ብለፋ አይሳካልኝም፡፡ እከሌ ተቀይሮብኛል ወዘተ የመሳሰሉት ሃሳቦች ናቸው፡፡ አፍራሽ አስተሳሰብ ያላቸው ሰወች ሃሳባቸው ውስጥ ችግር ይበዛበታል፡፡ ሁሉም ነገር እነሱ ላይ የባሰ ይመስላቸዋል፡፡ ሁላችንም ግን የተበደልንበት ጊዜ አለ፡፡ የሚያጠራጥር ሁኔታ ይገጥመናል፡፡ የማይታመኑ ሰወች አሉ፡፡ ሲቀርቧቸውም ሆነ ሲደውሉላቸው ግድ የማይላቸው ሰወች አሉ፡፡ ሰወች ሊቀየሩብን ይችላሉ፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ሁኔታወች በየጊዜው በሰማይና በመሬት መካከል የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ አዲስ ነገር አይደሉም፡፡ የህይወት አንዱ ክፍል ናቸው፡፡ በቃ፡፡ ትልቁ ጥያቄ ግን ይኸን ቀውጢ ሁኔታ እንዴት መቋቋም እንችላለን ነው፡፡ በዚህ ከተስማማን ጥሩ ምርጫወች አሉን፡፡
ለምሳሌ ሰወች ተቀየሩብን እንበል፡፡ መጀመሪያ ሰወች ዝም ብለው በድንገት አይቀየሩም፡፡ ምክንያት አላቸው፡፡ ሰወች ከተቀየሩብን በራሳችን ስህተት ጭምር ሊሆን ስለሚችል ማጣራት ይቀድማል፡፡ ብዙውን ጊዜ ሰወች የሚራራቁት በትንሽና እዚህ ግባ በማይባል ነገር ነው፡፡ ትንሿ ነገር ሳይታሰብ ትሰፋለች፡፡ ብዙ ሰወች ትንሿን ነገር ለማለፍ ይቸገራሉ፡፡ ወይም ሁል ጊዜ ትንሽና አንድ አይነት ስህተት በየጊዜ ይሰራሉ፡፡ ነግረዋቸውም አይሰሙም፡፡ ከተቻለ ቀስ ብሎ መነጋገር ነው፡፡ ይኸ የማይሰራ ከሆነ መተውና መርሳት ነው፡፡ አንዳንድ ሰወች ዘይት እንዳለቀበት ሞተር ነገር ነክሰው ከያዙ አይለቁም፡፡ በችግር ዙሪያ እያወሩ ከማለቃቀስ ይልቅ ስለ ችግሩ መፍትሄ መነጋገር የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ ወደፊት ማየትና መንቀሳቀስ ይሳናቸዋል፡፡ ህይወት ግን ትቀጥላለች፡፡ አፍራሽ ሃሳብ ያላቸውና ክብር የማያሳዩ ሰወች ጋር ደጋግሞ ጊዜ ማሳለፍ ቢያንስ ሰነፍና ሃሜተኛ ያደርጋል፡፡ ወደ ኋላ ይስባል ማለቴ ነው፡፡
አሁን መፍትሄው ምንድነው?
ለማጠቃለል ያህል፤ መጀመሪያ አፍራሽ አስተሳሰቦችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አይቻልም፡፡ ብዙውን አፍራሽ አስተሳሰብ ግን በገንቢ አስተሳሰብ መተካት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ሰው የምንጠራጠር ከሆነ ምክንያቱ እራሳችን ልንሆን እንችላለን፡፡ ነገሮችን አጣሞ የማየት አመል ካጠቃን ሁሉም ነገር ጠማማ አይደለም፡፡ አንድ አይነትና ተደጋጋሚ ስህተት ከሰራን ከራሱ ከህስተቱ ለመማር ፈቃደኛ መሆን ነው፡፡ የማይቻለውን ለመቻል ደጋግሞ መለማመድ ነው፡፡ የአንድ ሰው ደካማ ጎኖች ማንነቱን ሙሉ በሙሉ አይወክሉም፡፡ ሁላችንም ደካማ ጎን አለን፡፡ ሰወች ላይ፤ እያንዳንዷን ትንሽ ስህተት ከ ሀ እስከ ፐ ድረስ መከታተል ብዙ ትርፍ የለውም፡፡ ዝናብ እየጣለ የጨፈገገ ቀን ከሆነ ቢያንስ ለዕጸዋቶቹ፣ ለአየሩ ጽዳት፣ ለአርሶ አደሮች፣ ወዘተ ይፈለጋል ብሎ ማሰቡ ቆንጆ ይመስለኛል፡፡ በዝናቡ መሃል ወይም ሌላ ቀን ላይ ጸሀይ ትወጣለች፡፡ ለፍቼ፤ ለፍቼ አይሳካልኝም ካልን ደግሞ ህይወት በሙከራና በልፋት የተሞላች ነች፡፡ በተለይ ጥሩ ውጤት በነጻ አይገኝም፡፡ በዙሪያችን የሚታዩ ነገሮች ለስኬትና ለውድቀት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ምናልባት የተፈለገው ውጤት ላይ ለመድረስ የተሄደበትን መንገድና አሰራር መከለስና አሻሽሎ መቀጠል አንዱ ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ ማንም ሰው ቢሆን ግን ለብቻው ለችግርም ሆነ ለደስታ ተመርጦ አልተፈጠረም፡፡
አንድ ሰው ጠንካራና ደካማ ጎኑን ለይቶ ካወቀ ህይወት ትቀለዋለች፡፡ ለምሳሌ የኔ ከፍተኛ ደካማ ጎን፤ ነገር ቶሎ አይገባኝም፡፡ ፈጣን አይደለሁም፡፡ ያልፈኛል፡፡ የሚያውቁኝ ወዳጆቼ ያውቁታል፡፡ ሁሉም ቦታና ሁኔታ ላይ ግን አይደለም፡፡ አንዳንድ ጠንካራ ጎኖቼን መናገር ከተፈቀደልኝ ደግሞ፤ ከአፌ መጥፎ ቃላት እንዳይወጡ በጣም እጠነቀቃለሁ፡፡ ይኸን የማደርገው ሰወች እንዳይጠሉኝ አይደለም፡፡ ለራሴ ህሊና ነው፡፡ ሰወች እንዲወዱኝ ብየ መስማት የሚፈልጉትን መናገር አልፈልግም፡፡ እኔ አጥብቄ የምፈልገው ሰወች ጋር ለመግባበት እንጂ ይወዱኛል ብየ አልጠብቅም፡፡ የሰወችን ሞራል መጠበቅና መገንባት እወዳለሁ፡፡ የሞኝና የደግነት ልዩነት ምን እንደሆነ አጥብቄ የማውቅ ይመስለኛል፡፡ ምሳሌውን በኔ ላይ አድርጌ የጠቀስሁት፤ አንድ ሰው ደካማና ጠንካራ ጎኑን ካወቀ አፍራሽ ነገሮች ላይ ትኩረቱ ይቀንሳል ብየ ስለማምን ነው፡፡ ደካማ ጎን ማሻሻል ይቻላል፡፡ ጠንካራ ጎን ላይ ጠበብት መሆን ይቻላል፡፡ ጠበብት መሆን ማለት አንድ ሰው በሚችለው ነገር ላይ ገትሮና ደጋግሞ ከሰራ በኋላ በገሃድ ማሳየት ሲችል ነው፡፡ ሌላ ሚስጥር የለውም፡፡ አንድ ሰው ጠበብት ለመሆን ዶክተር መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ማንኛውም ሰው በየትኛውም መስክ ጠበብት መሆን ይችላል፡፡ ጠበብት የመሆን ፍላጎት ተከታይ ብቻ ከመሆን ያድናል፡፡ ሰው ሁልጊዜ ለማጅ መሆን የለበትም፡፡ በሚወዱት ነገር ላይ ጠበብት ለመሆን ካሉት ዘዴወች አንዱ እንደሚከተለው ነው፡፡
ህብረተሰቡ ውስጥ መልካም ከሚያስቡ ሰወች ተርታ መሰለፍ እችላለሁ ብሎ እራስን ማሳመን መብራት ያሳያል፡፡ በተለይ ጥሩ በማሰብ አንደኛ መሆን እችላለሁ ብሎ ማመን በራሱ ወደ ፍጹምነት ያስጠጋል፡፡ ለዚህ ቦታ ከሰጠነው እረዢም እርቀት መሄድ እንችላለን፡፡
This policy contains information about your privacy. By posting, you are declaring that you understand this policy:
This policy is subject to change at any time and without notice.
These terms and conditions contain rules about posting comments. By submitting a comment, you are declaring that you agree with these rules:
Failure to comply with these rules may result in being banned from submitting further comments.
These terms and conditions are subject to change at any time and without notice.
የተሰጡ አስተያየቶች