ማውራትና መጠየቅ ብቻውን ሙሉ አያረግም፡፡ አንድ ሰው ሁሉንም ጥያቄ መፍጠር አይችልም፡፡ አንድ ሰው ለሁሉም ነገር መልስ ሊኖረው አይችልም፡፡ የሆነ ነገር ተጠይቀን የማናውቀው ከሆነ፤ ደፍረን አላውቀውም ማለት ይሻላል፡፡ እኔ ይኸን አሁን አላውቀም፡፡ ወደፊት ግን ማወቅ እፈልጋለሁ የሚል አስተሳሰብ ያዳበረ ሰው የተሻለ ነገር እንዲያውቅ በራሱ ያነሳሳዋል፡፡ ለምሳሌ፤ አሁን እኔ የማላውቀው ነገር ካለ ለማወቅ ፍላጎት ሊኖረኝ ይገባል፡፡ ፍላጎቴን ለማሳካት ግን ያሉትን መንገዶችና ዘዴዎች ለመጠቀም በራሴ መልፋት አለብኝ፡፡ ሰው በራሱ አስቦ ወይም ሰርቶ የደረሰበትና የተለማመደበት ነገር ቶሎ አይረሳውም፡፡ በራሴ ካልቻልሁ ደሞ ሰው መጠየቅ እችላለሁ፡፡ ስጠይቅ ግን እንዴት እንዳሰብሁና ምን እንደፈለኩ መጀመሪያ እራሴን ግልጽ ማድረግ ጥያቄየን ግልጽ ያደርገዋል፡፡ እኔም ዝም ብየ ለመጠየቅ ብቻ የተነሳሁ አይመስልብኝም፡፡
ለምሳሌ ለጊዜው የማይታወቁን ሃሳቦች ሁለት አይነት ናቸው እንበል፡፡
1ኛ) ውጫዊ ጥያቄ ነው፡፡
2ኛ) ውስጣዊ ጥያቄ ነው፡፡
የመጀመሪያው ጥያቄ፤ ሰው በቀጥታ ጠይቆን መልስ ሳይኖረን ሲቀር ነው፡፡ ውጫዊ ጥያቄ ሌላ ሰው የሚጠይቀን ጥያቄ ነው ማለት ነው፡፡ የማናውቀው ከሆነ ባደባባይ ወይም ፊት ለፊት አላውቅም ማለት ያሳፍራል ብየ አላስብም፡፡ አንድ ሰው ሁሉንም ነገር ማወቅ አይችልም፡፡ ለጊዜው አላውቅም፤ ይኸን ነገር ወደፊት ፈልጌ ማወቄ ግን አይቀርም ብሎ መመለስ ይሻላል፡፡ ይኸ አንድ አማራጭ ዘዴ ነው፡፡ ይኸ ዘዴ ግን ተስማሚ የሚሆነው ጥያቄው ጊዜ የሚሰጥ ከሆነ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰወች አላውቅም ማለት የሚያሳፍራቸው ይመስላቸዋል፡፡ የዚህ አይነት ስሜት በሚሰማን ጊዜ ግን ዘዴ መጠቀም እንችላለን፡፡ በተለይ ጉዳዩ ጊዜ የሚሰጥ ከሆነ፤ አሁን አላውቀውም፤ ግን አስብበታለሁ፤ ብሎ ቆዳ መሸፈን የተሻለ ምርጫ ነው፡፡ በማናውቀው ጉዳይና ሰው ላይ ትንተና ውስጥ ከገባን ግን ዞሮ ዞሮ በኋላ እውነቱ ይወጣል፡፡ በኋላ እውነቱ ሲታወቅ መጀመሪያውኑ ባስብበት ኖሮ ማለት ይናፍቃል፡፡
ለዚህም ነው ሰወች በቃላቸው መገኘት የሚከብዳቸው፡፡ ሰው ካሳሳቱ በኋላ በይቅርታ የሚጠገን የሚመስላቸው፡፡ ሰማይ ጠቀስ መሆናቸውን አሳውቀው እውነቱ ሲወጣ መሬት ላይ ዘጥ የሚሉት፡፡ በርግጥ ብዙ ነገሮች ከጊዜ ጋር መልክ ይቀይራሉ፡፡ መሰረተ ሃሳባቸው ግን ቀጥ ያለ ነው፡፡ ለምሳሌ ልክ ፀሃይ በምስራቅ ወጥታ በምእራብ ትጠልቃለች፡፡ አቅጣጫና ኢላማዋ የታወቀና አንድ ነው፡፡ ቀን ላይ ግን በጉምና በደመና ምክንያት ላታሞቅ ትችላለች፡፡ ልትሸፈን ትችላለች፡፡ በተከታታይ ላናያት እንችላለን፡፡ አቅጣጫዋን ግን አትስትም፡፡ ሰውም በቃሉ ለመገኘት ካልተወው በስተቀር የሚያግደው የለም፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ሰው ሳይጠይቀን በውስጣችን የሚሰማ ነው፡፡ ሁኔታዊ፣ ወቅታዊና ህይወታዊ ጥያቄወች በውስጣችን ሃሳብ ይጭራሉ፡፡ ለምሳሌ የሆነ ነገር ለመገጣጠም ሊሆን ይችላል፡፡ በህይወታችን ውስጥ ምን እንደምንፈልግ የምናስበው ሊሆን ይችላል፡፡ አስበን የደረስንበትን ነገር ደግሞ እንዴት መፈጸም እንደሚቻል እቅድ ስናወጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ውስጣዊ ጥያቄ በአብዛኛው ገና መፍትሄ ያላገኙ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የኑሮ ሁኔታን መሰረት አድርገን እራሳችን በራሳችን የምንጠይቀው ጥያቄ ነው፡፡ ውስጣዊ ጥያቄ በአደባባይ የሚጨህ አይደለም፡፡ አስፈላጊና አጣዳፊ ከሆነ ወዲያውኑ በራሳችን መንቀሳቀስ እንችላለን፡፡ ጊዜ የሚሰጥ ከሆነ ደግሞ፤ ከጊዜ ጋር በመስራትና በማሰላሰል እንደርስበታለን፡፡
የተጠቀኳቸው ዘዴወች በማናውቀው ነገር ላይ ያወቅን መስለን ከመቅረብ ይልቅ ለማወቅ ፍላጎት እንዲኖረን ይረዱናል ብየ አስባለሁ፡፡
This policy contains information about your privacy. By posting, you are declaring that you understand this policy:
This policy is subject to change at any time and without notice.
These terms and conditions contain rules about posting comments. By submitting a comment, you are declaring that you agree with these rules:
Failure to comply with these rules may result in being banned from submitting further comments.
These terms and conditions are subject to change at any time and without notice.
የተሰጡ አስተያየቶች