mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

ዝርክርክ ባህሪ እና ትክክለኛ አጠቃቀም

mejemer computer proper usage

ብዙ ዊንዶውስ ተጠቃሚወች በተለይ የኢትዮጵያውያን ችግር ያጠቃቀም ባህሪ ለችግር ያጋልጣቸዋል። ይኸንን እኔ በአይኔ አይቻለሁ፡፡ ነጻ የሆኑ ሶፍትዌሮችን ሳያጣሩ መሰብሰብና ማግበስበስ ያስጠቃል። በተለይ ከሙከራ ሶፍትዌር ጋር ማስታወቂያ ይጨምሩበታል። ይኸን ማስታወቂያ በኋላ ማስወጣት በጣም አስቸጋሪ ነው። የት ሄዶ እንደሚቀመጥ አይታወቅም። እነዚህ ለዊንዶውስ የተሰሩ አብዛኛወቹ የነጻ ሶፍትዌሮች አላማ አላቸው። ጥሩ የነጻ ሶፍትዌሮች ቢኖሩም ማጣራት ያስፈልጋል። የቤቱን በራፍ ብርግድ አድርጎ ከፍቶ የማያውቀውን ሰው ወደ ቤቱ የሚያስገባ የለም። እኔ ኢትዮጵያዊ በባህሌ እንግዳ ማስተናገድ አይቸግረኝም ለሚል ሰው ኮምፕዩተርን በተመለከተ አያዋጣም!!

የነጻና ጠቃሚ መስለው ኮምፕዩተሩን ለማበላሸት ወይም ተጠቃሚው ምን አይነት እንቅስቃሴ እንዳለው ለመሰለል የሚላኩ ሶፍትዌሮች አሉ። ለምሳሌ የተጠቃሚውን እንቅስቃሴ ካወቁ በኋላ የሚፈልጉት ማስታወቂያ እየላኩ ለማስቸገር ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለላ ከሆነ ደግሞ ተጠቃሚው ምን እንደሚያደርግ ለመከታተልና ከተሳካም የተጠቃሚውን ኮምፕዩተር ለመጥለፍ ወይም ያለውን ሰነድ ለመስረቅ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡

ይኸ የሚደርሰው ግን ተጠቃሚው ሳያጣራ ወይም በግደለሽነት እነዚህ ጎጂ ሶፍትዌሮች ኮምፕዩተሩ ላይ እንዲሰፍሩ ስለሚፈቅድ ነው። ጎጂ ሶፍትዌሮች ሳይፈቀድላቸው በራሳቸው ለመግባት በመርፌ ቀዳዳ ግመል እንደሚባለው ነው። ለዚህም ነው የተጠቃሚው ያጠቃቀም ባህሪ ግደለሽ ከሆነ በኋላ ዋጋ ያስከፍለዋል፡፡ ምክንያቱም ብዙው ሰው የነጻ ሶፍትዌር ሲባል ከበስተጀርባው ምን እንዳለበት አይገምትም። ነጻ ስለሆነ ብቻ መጠቀም ይፈልጋል። ለጓደኛም የነጻ ፕሮግራም አለ ተጠቀምበት ብሎ መንገር የተለመደ ነው። ጉዳቱ ግን አይታይም። ኢትዮጵያዊማ ከሆነ እንኳን ሶፍትዌር ቀርቶ ሳይሰራ እንኳን በነጻ ነጻ እሆናለሁ ብሎ የሚያልም ጥቂት አይደለም።

ሌላው ደግሞ ይለፍ ቃል የሌለበት ክፍት የሆነ የነጻ ኢንተርኔት አገልግሎት መጠቀም አንዱ የመጠቂያ መንገድ ነው። ነጻ ያደረጉት ዝም ብለው አይደለም። ሁሉም ባይሆንም የሆነ ተንኮልና ማባበያ አለበት። አንዳንድ አቅራቢወች ኢንተርኔቱን በበጎ ፈቃድ ክፍት ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ችግሩ ያለው ግን ይኸን በጎ ፈቃድ ተጠቅመው ሌሎች ለተንኮል የሚያፈነፍኑ ስላሉ ነው፡፡ ሌላው የመጠቂያ መንገድ ደግሞ ካልታወቀ ቦታ በኢሜይል ተያያዘው የሚመጡ ሰነዶች ናቸው።

ተያያዡ ከታማኝ ወይም ከተጠበቀ ምንጭ መሆኑን ሳያጣሩ መክፈት ተጨማሪ ማስታወቂያ እንዲመጣ መንገር ነው። ሲከፋ ደግሞ ተያያዡ ምናልባት የስለላና የስርቆት ሶፍትዌር ሊሆን ይችላል፡፡ ተያያዡን ሲከፍቱት ደግሞ ተባይ የያዘ ሰነድ ከሆነ ወዲያውኑ የተጠቃሚው ኮምፕዩተር በተባይ ሊለከፍ ይችላል። ኮምፕዩተሩ ለስለላ የተመቻቸ ሊሆን ይችላል። ከእውነተኛ አድራሻና ታማኝ መስለው ቀርበው የግል መራጃንም የሚጠይቁ አሉ። ለዚህ ሁሉ ተጠቃሚው መጠንቀቅ አልበት እንጅ ዝም ብሎ የግል መረጃ በጭራሽ መስጠት የለበትም። እዚህ ጋ ተጠቃሚው እራሱን መጠበቅ ከፈለገ ያልታወቀና ያልተጠበቀ ወይም ጥርጣሬ ያለበትን መልክት መክፈት ወይም ምላሽ መጠት የለበትም። አንዳንድ ሰወች ኮምፕዩተራቸው ከተለከፈ ወይም መለከፉን ሲጠራጠሩ አዲስ ኮምፕዩተር መግዛት ከችግራቸው የሚያድናቸው ይመስላቸዋል። ዞሮ ዞሮ ኮምፕዩተሩን የሚጠቀምበት ሰው ባህሪው ያው እስከሆነ ድረስ ጉልቻ ቢቀየር ወጥ አያጣፍጥም። ያንኑ የተለከፈውን ኮምፕዩተር እንደገና አዘጋጅቶና ገንዘብም ቆጥቦ መኖር ይቻላል።

ኢንተርኔት መቅዘፊያው ቅድሚያ ዝግጅት ካልተደረገለት ለምሳሌ የጂሜይል ይለፍ ቃልህን ላስታውስልህ ወይ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። ተጠቃሚው በስንፍናም ይሁን ባለማወቅ "እሺ"ብሎ ከመለሰለት በሚቀጥለው ጊዜ በቀጥታ ይገባል። ተጠቃሚው ይህን በሚያደርግ ጊዜ ይለፍ ቃሉ በማን እንደታየ መቆጣጠር አይችልም። ኮምፕዩተሩን በማይጠቀሙበት ጊዜ ደግሞ ከገቡበት ሳይወጡ የሚተውም አሉ። ኮምፕዩተሩንም ሲርቁ ሳይወጡ ወይም ሳይዘጉት የሚሄዱ አሉ። ሰው ቤቱን ከፍቶ ወደ ገበያ አይሄድም!! ጥቂት የማይባሉ ሰወች በተመሳሳይ ሞኝ አመላቸው እንዲጠቁ ያደርጋቸዋል። ለነገሩ ሰወች ግል ኮምፕዩተራቸውን ሲጠቀሙ ባህሪያቸውን ካሳመሩ አንቲቫይረስ እንኳን ላያስፈልጋቸው ይችላል። ከሁሉም በላይ ግን ሰወች ሊኑክስ እንዲሞክሩ እመክራለሁ። ሊኑክስን ለመውደድ ቀላል ነው። እንደዚህ ተከፋፍሎ በቅደም ተከተልና በመልኩ ስለቀረበ አንባቢወች እንደሚወዱትና እንደሚከታተሉ ተስፋ አለኝ።

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!