mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

የሞባይል ስልክ ክፍል 2፤ አፖችና ቀዳዳቸው

ባይል ስልካችን፤ ለሳይበር ጠላፊዎች በተለያዩ መንገዶች ተደራሽ ነው። ከብዙዎቹ አንዱ የመጠቂያ ቀዳዳ፤ ነጻ የሆነ እና በትክክል ከየት እንደሆነ ያልታወቀ አፕ፤ ስልካችን ላይ የመጫን ባህሪ ለምዶብን ከሆነ ነው። ብዙዎቹ የነጻ አፖች፤ አስተማማኝ አይደሉም። ስልካችን ላይ ከሰረጉ በኋላ፤ ከበስተጀርባ ምን አይነት ስስ መረጃ፤ አሳልፈው እንደሚሰጡ አይታወቅም። በተለይ፤ ምንጫቸው ያልታወቁ አፖች አደጋ አላቸው።

አብዛኛዎቹ የነጻ አፖች፤ ማስታወቂያ ይጨምሩበታል። ማስታወቂያው፤ ምን አይነት ስስ መረጃ እንደሚያቀብል፤ በውል አይታወቅም። ምናልባት የታወቁ ድረጅቶች፤ የሚያቀርቧቸው ነጻ የሆኑ አፖች፤ ትንሽ ይሻላሉ ይሆናል። ዞሮ ዞሮ ግን፤ እነዚህም ቢሆኑ፤ ምን አይነት ስስ የሆነ የግል መረጃ እንደሚፈልጉ፤ ተጠቃሚው ማወቅ አለበት። ለምሳሌ፤ ማንኛውም አፕ መስራት ከመጀመሩ በፊት፤ ስልካችን ውስጥ ካለው የግል ነገር ጋር፤ ግንኙነት ማድረግ ይፈልጋል። ዝም ብሎ፤ በራሱ ለብቻው አይሰራም። ከስልኩ ባለቤት ጋር ሳይሆን፤ ከስልኩ ውስጥ ካለው ኦፕሬቲንግ ሲስተም ጋር፤ መገናኘት ይፈልጋል። ከዛ በኋላ፤ ለምሳሌ ከካሜራ፤ ከጂፒኤስ፤ ከኮንታክት ስምና ስልክ፤ ከኢሜይል አድራሻ ጋር፤ መዛመድ ይፈልጋል። ዝምድናውን ከመጀመሩ በፊት፤ በትክክል ለመስራት ይቸገራል። ተጠቃሚው፤ አፑን ካመነውና አላማው ለምን እንደሆነ ካወቀ በኋላ፤ አስፈላጊውን ፈቃድ ብቻ መስጠት አለበት። የዚህን ያህል አስፈላጊ ካልሆነ፤ ጭራሹኑ አለማስገባት ይሻላል። የሚሸጡ አፖችም አሉ። አብዛኛዎቹ አፖች ደግሞ፤ ዋጋቸው ርካሽ ነው። እንደ ነጻዎቹ ማስታወቂያ አያስገቡም።

ሞባይል ስልከዎን ደህንነት መጠበቅ ማለት፤ የማያውቁትን ሰው፤ ወደ ቤትዎ ከመጋበዝ ያለፈ ነው። የጋበዙትን ሰው ከሆነ፤ በአካል ያዩታል። በአካል እያዩ ይቀበሉታል። ከግብዢያ በኋላ ደግሞ፤ በአካል እያዩ ይሰናበቱታል። እንዳውም ከቤትዎ የጋበዙት ሰው ሆዱ ሞልቶ ሲወጣ፤ እርስዎ ደግሞ ፈገግ ሲሉ፤ እሱ ደግሞ ወጥ ወጥ እየሸተተ ወደ ቤቱ ይመለሳል። አፕ ከሆነ ግን፤ ስልከዎ ላይ ሲገባና ከገባ በኋላ፤ ስልክዎ ውስጥ እያፈነፈነ፤ ምን እንደሚያደርግ በግልጽ አይታወቅም። የሚፈልጉትን ተግባር በስልክዎ ለማካሄድ፤ የሆነ አፕ በሚፈልጉ ጊዜ፤ መጀመሪያ አፑን ከመጫንዎ በፊት ማን እንደሰራው፤ የቻሉትን ያህል ቢያጣሩ፤ ከመውደቅ እራስዎን ያድናሉ። አፑን ሲጭኑት ደግሞ፤ ከየትኛው ስስ መረጃ ጋር፤ ግንኙነት እንደሚያደርግ፤ ማወቅ አለብዎት።

ከሆነ ጊዜ በኋላ ደግሞ፤ አፑ አስፈለጊ ካልሆነ፤ ማስወጣት ይሻላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ፤ ስልክዎ ላይ እየነካኩና ወዲያ ወዲህ እያሉ፤ አፖቹ የት እንዳሉ ለማወቅ ጊዜ ይጠቀሙ። ምን አይነት አፕ፤ ስንት አፖች እንዳለወት ማወቅ ይችላሉ። በመሰረቱ፤ መቆጣጠሪያ ቦታው የት እንዳለ ማወቅ፤ እጅግ በጣም ይጠቅማል። በየጊዜው ተጨማሪ ጥንቃቄ ማድረግ አለብዎት! ከዛሬው ጥሩ ማሳሰቢያ ጋር፤ መልካም ውሎ!

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!