mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

ከማመልከቻ በፊት ቅድመ ዝግጂት

mejemer get the job prepare

ስደት የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ከልብ የፈለግነውና የተመኘነው የስራ አይነት በሙያችን እንዲናገኝ ለማድረግ የተለያዩ እንቅፋቶች ያጋጥሙናል፡፡ በተለይ የመኖሪያ ፈቃድ የሌለን በምንሆን ጊዜ ደህና የሆነ ስራ በሙያችን ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ በዚህም ላይ ደግሞ ጸጉረ ልውጦች ስለሆን ቀጣሪዎች ይጠራጠራሉ፡፡ ቀጣሪዎች እኛን ስራ ለመስጠት ቢፈልጉ እንኳን ያገሬው ሰራተኞች አይፈልጉ ይሆናል በማለት ለመቀጠር የሚተውበት ጊዜ አለ፡፡

አብዛኛው ስራ የሚገኘውም በዝምድና፣ በትውውቅና በጓደኝነት ነው፡፡ ከዛ የተረፈ የስራ አይነት ማስታወቂያ ላይ ይወጣል። ትውውቅና ጓደኝነት ለማፍራት አጋጣሚው መፈጠር አለበት፡፡ ይኸን አጋጣሚ እራሳችን ከጊዜ ጋር ለመፍጠር ሊሳካም ላይሳካም ይችላል።

በተጨማሪ ስዴት ላይ ሆኖ ተስማሚና የሚወደድ ስራ ለማግኘት ሂደቱ ውስብስብ ነው፡፡ እያንዳንዳችን ግን ስራ ለማግኘት ተጨማሪ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ታዲያ ይህንን ውስብስብ የሆነ ጉዞ እንዴት እንወጣዋለን? ስራ የማግኘት እድላችን እንዴት እንዲሰፋ ማድረግ እንችላለን?
ያገሩን ባህልና ቋንቋ ከሞላ ጎደል መቻል፣ የህዝቡን ያኗኗርና የአቀራረብ ዘይቤ ማወቅ ተወዳጁን ስራ ለማግኘት ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ይኸን ስሌት ማወቅና መረዳት አይደለም ስራ ማግኘት፤ በግል ህይወትና የማህበራዊ ትስስር ህይወታችን ውስጥ በዕውቀት እንዲንዳብር ያግዘናል፡፡

በትውውቅ፣ በጓደኝነትና በዝምድና ተይዘው ያላለቁ ክፍት የስራ ቦታዎች ማስታዎቂያ ላይ ይወጣሉ፡፡ ማስታወቂያው ጋዜጣ፣ መጽሄት፣ ኢንተርኔት ወዘት ላይ ሊሆን ይችላል። በማስታወቂያው ላይ ስለመስሪያ ቤቱ፣ ስለ ስራው አይነት፣ ምን አይነት የስራ ልምድ ያለው ሰራተኛ እንደሚፈለግ ባጭሩ ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ አመልካቾችም ለተጨማሪ መረጃ ማንን ማናገር እንደሚቻል ከስልክ ቁጥር ጋር ይገለጻል፡፡

ይኸን አጭር የስራ ማስታወቂያ በጥንቃቄ ረጋ ብሎ ማንበብና መረዳት በጣም ይጠቅማል፡፡ ማስታወቂያውን አንብበው ወዲያውኑ ማመልከቻ ከጻፉ ስራ የማግኘትዎ እድል በጣም አነስተኛ ነው። ከዛ በፊት ግን በቅድሚያ ማድረግ ያለብዎትን ነገሮች በዝርዝር እናያለን፡፡ ምክንያቱም ማስታወቂያው ላይ በተገኘው መረጃ ብቻ ማመልከቻ መላክ ስራውን ማግኘት ቀርቶ ለቃለ ምልልስ እንኳን ለመጠራት እድሉ ጠባብ ነው፡፡

አንድ የስራ ማስታወቂያ በወጣ ጊዜ በአስሮችና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰወች ያመለክታሉ፡፡ የአመልካቾች ቁጥር በጨመረ ቁጥር ውድድሩም ይብሳል፡፡ ታዲያ ማስታወቂያውን አንብበው በደንብ ከተረዱ በኋላ ወደ መስሪያ ቤቱ ደውለው የሚመለከተውን ግለሰብ ማናገር ይጠቅማል፡፡ ከመደወልዎ በፊት ዝግጅ ማድረግ አለብዎት፡፡ ሲደውሉም ስልኩ በጸሃፊ ከተነሳ ማን እንደሆኑ፣ ለምን እንደሚደውሉና ከማን ጋር መነጋገር እንደሚፈልጉ ባጭሩ መግለጽ ተገቢ ነው፡፡

ማስታወሻ!
አንዳንድ ስራ ቀጣሪዎች እጩ ሰራተኛ ለማግኘት ደላላ ወይም "አዕምሮ አዳኞች" የሚባሉ ጋር ግንኙነት አላቸው። የዚህ አይነት ሁኔታ ካለ እዛው ማስታወቂያው ላይ ያገኙታል። ስለዚህ እርስዎ በቀጥታ ወደ ቀጣሪውም ሆነ ደላላው ዘንድ ከደወሉ የት እንደሚደውሉና ከማን ጋር እንደሚነጋገሩ ቢለያይም የስልቱ አይነት ግን ይመሳሰላል፡፡

ማነጋገር ከሚፈልጉት ግለሰብ ጋር በተገናኙ ጊዜ፤ “ እንደምን ዋሉ! ስሜ እከሌ ይባላል፡፡ የምደውለው ከዚህ ቦታ ነው፡፡ የመጣሁት ከዚህ አገር ነው (እንደ ሁኔታው ቢለያይም ይኸን ማሳወቅ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም።) ያወጡትን የስራ ማስታዎቂያ አይቸዋለሁ፡፡ ስራው ይህንንና ይህንን ስለሚመስል እኔም የዚህ አይነት ልምድ ወይም ፍላጎት ስላለኝ ይስማማኛል፡፡ ማመልከቻም ለመላክ አስቤአለሁ፤ ” ካሉ በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎችን ይጠይቁ፡፡ ይኸ የስልክ ንግግር በሚካሄድበት ጊዜ ረጋና ቀስ ብለው ባጭሩና በግልጽ ቋንቋ ቢናገሩ ሰሚው በቀላሉ ይረዳዎታል፡፡ በመካከል ሰሚው በሚናገር ጊዜ እንዳያቋርጡት ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ የዚህ ንግግር አላማ ማመልከቻ ከመላክዎ በፊት እርስዎን ባጭሩ ለማስተዋወቅ ነው እንጂ ብዙ ወሬና ኮተት አያብዙ፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ባጭሩ ጥሩ ትዝታ ጥለውና አመስግነው ንግግሩን ለመጨረስ ይሞክሩ፡፡ ያናገሩትን ሰው ስምና ቀኑን ያስታውሱ!

ማመልከቻ አጻጻፍ፣ ሂደቱና ክትትሉ ቀጣዩ ገጽ ላይ፤

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

Avatar
New
selamawit gutasays...

በጣም ጠቃሚ እውቀት አግኝቼበታለው በርታ ወገንህን ለማገልገል በመጣርህ ልትመስገን ይገባሃል በርታ

Admin:

አመሰግናለሁ መልካም ሰንበት