የተለያዩ አቀራረቦች አሉ፡፡ ማንም ቢሆን ግን ለዛ ያለውና ቀና የሆነ አቀራረብ ይመርጣል። ልብ ለሚል ሰው መጥፎ ነገር ቀርቶ መልካም ነገር ላይ እንኳን ሲያስቡ፣ ሲናገሩና ሲመለከቱ ሳያውቁት ፊታቸው መኮሳተር የለመደባቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም። በጊዜው ለኛ ባይታየንም ተመልካች ግን ያውቀዋል፡፡
የመጀመሪያ ግምገማ ወሳኝ ስለሆነ ስራ ፍለጋ ሄደው ፊትዎን አኮሳትረው እራስዎን እንዳይቀጡ፡፡ አደራ፡፡ ሲናገሩና ሲያስቡ ፊትዎ ምን እንደሚመስል በመስታወት ወይም በጓዴኛ ቀድመው መለማመድ ይችላሉ፡፡
ለቃለ መጠይቅ የሚሄድበትን ቦታ ቀደም ብሎ አድራሻውን ማወቅ ከሃሳብና ጭንቀት ያድናል፡፡ በቀጠሮውም ሳይዘገዩ አምስት ደቂቃ አካባቢ ሲቀረው በቦታው መገኘት የተሻለ ምርጫ ነው፡፡ እጅዎንም ካላበዎት በመሃረም ነገር ያድርቁት፡፡ በነገር የሚያፋጥጡ ቀጣሪዎች ጋር ሰላምታ ሲቀያየሩ አንገትዎን ቀና፣ ፊትዎንና ትካሻዎን ዘና አድርገው ፊት ለፊት እያዩ ጠበቅና ሞቅ ያለ ሰላምታ መስጠት አለብዎት፡፡ ከዚህ በፊት በስልክ ያነጋገሩት ግለሰብ መጥቶ ከተቀበለዎት እና በስሙ እርግጠኛ ከሆኑ፤ “ከርስዎ ጋር ከዚህ በፊት ስለስራው ተነጋግረናል” ብሎ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የማስታወስ ችሎታ ማሳየት አይከፋም፡፡
ወደ ውይይት ክፍሉ ሲሄዱ መተላለፊያው፣ መታጠፊያውና በሮች የበዛበት ከሆነ፤ በኋላ ሲወጡ መውጫው እንዳይጠፋዎት ልብ ይበሉ፡፡ ምናልባት የሚሸኝዎት ሰው አብሮ ላይሆን ይችላል፡፡ መውጫ መንገዱን ማስታወስ በኋላ ከትዝብት ያድናል፡፡ እኔ አንድ ጊዜ መውጫ በሩ ጠፍቶኝ ተሸውጄ አውቃለሁ፡፡ በኋላ ላይ እራሴን በመዳፌ እየመታሁ አንተ ደንቆሮ ብየዋለሁ፡፡ ግን ትምህርት ብቻ መውሰድ ነው እንጂ ምንም ጥቅም የለውም፡፡
ክፍሉ ውስጥ እንደገቡ ሌሎች ሁለት አካባቢ የሚሆኑ በነገር የሚያፋጥጡ ግለሰቦች መኖራቸው አይቀርም፡፡ ለነሱም ሞቅ ያለ ሰላምታ ያቅርቡ፡፡ ስማቸውንም ለማስተዎስ ይሞክሩ፡፡ ክፍሉ ጥሩ ከሆነ ለምሳሌ ጠረንጴዛው በደንብ የተሰናዳ ከሆነ ወይም ግድግዳው ላይ ጥሩ ስዕል ተሰቅሎ ከሆነ፤ ጥሩ መሆኑን እያደነቁ ከጠቀሱ ጥሩ ታዛቢ መሆንዎን ያሳያል፡፡ የማያምር ከሆነ ግን ማስመሰል ስለሆነ አፍዎን አያበላሹ፡፡ ብዙውን ጊዜ ግን የሆነ የሚደነቅ ነገር አይጠፋም፡፡ ሲቀመጡ ሌሎቹን መጀመሪያ ማስቀደም ተገቢ ነው፡፡
ከተቀመጡ በኋላ ተዝናንተው በስርአት ይቀመጡ እንጂ ዝልፍልፍ አይበሉ፡፡ የፈሩም አይምሰሉ፡፡ እግርዎን ሳያነባብሩ ቁጭ ብለው እጆችዎ ጭነዎ ላይ አርፈው አገጭዎ ፎቶ እነደሚነሳ ሰው ቀና ብሎ፤ ትካሻዎና ወገብዎ ሲዝናና ከተሰማዎት ግሩም አቀማመጥ ይመስለኛል፡፡ ፊትዎ ዘና ማለቱን ሁልጊዜ ያስታውሱ። ይህ አቀማመጥ እንደተጠበቀ ከሆነ እጅና ሰውነት በቀላሉ ለማንቀሳቀስ ምቹ ነው፡፡ ምናልባት ለመተንፈስም ይረዳል፡፡ በሚናገሩ ጊዜ የጠየቀዎትን ግለሰብ በቀጥታ እያዩ ቢሆንም ሌሎቹንም ለአፍታ አየት ማድረግ አለብዎት፡፡ ቀጣሪዎቹ በሚናገሩ ጊዜ እንዳያቋርጡ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ አቀርቅረው አያውሩ፡፡
የሚናገሩት ቋንቋ ያልተቀላቀለ፣ ግልፅና ሙሉ መሆን አለበት፡፡ አፉን እንደሚፈታ ህጻን ልጅ መንተባተብ አይገባም፡፡ ቀጣሪዎቹ “ምን አሉ?” እንዲሉዎት እድል አይስጡ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር እጅዎን አያወናጭፉ፡፡ ነገር ባጭሩ ይመልሱ እንጂ ያለአስፈላጊ ብዙ ትንተና ውስጥ መግባት ነገር ያበላሻል፡፡ የማያውቁትን ነገር ከተጠየቁ “ይኸን አላውቅም” ማለት ይሻላል፡፡ ሲያዳምጡም ሆነ ሲናገሩ የፊትዎ ገጽታ የዘና የተዝናና መሆኑን በውስጥዎ ያስታውሱ፡፡ አቀራረብ!! በተረፈ የሚጠበቁ ጥያቄዎች ምን እንደሚመስሉ ባለፈው ክፍል 6 ላይ አቅርቤአለሁ፡፡
ቃለ መጠይቁ እንዳለቀ ካመሰገኑ በኋላ ውልቅ ብሎ መውጣት ነው፡፡ ውጤቱ በቀናት ወይም በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ይታወቃል፡፡ መልካም እድል!!
ስራውን ካገኙት በኋላ ምን አይነት የተጻፈና ያልተጻፈ ህግ መከተል እንደሚቻል ክፍል 8 ላይ አቅርቤአለሁ። ክፍል 8 የመጨረሻው ነው፡፡ ይቅናዎት!
This policy contains information about your privacy. By posting, you are declaring that you understand this policy:
This policy is subject to change at any time and without notice.
These terms and conditions contain rules about posting comments. By submitting a comment, you are declaring that you agree with these rules:
Failure to comply with these rules may result in being banned from submitting further comments.
These terms and conditions are subject to change at any time and without notice.
የተሰጡ አስተያየቶች