mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

ለሚያስብ አዕምሮ

mejemer ethiopia amharic መጀመር ኢትዮጵያ ፋንታው ተሰማ አማርኛ

ዕምሮ ካሰበ እጃችን ሲዘረጋ ጥፋት አያበዛም። ልባችን ሲከፈት ልከኛ ርህራሄ ያሳያል። አፋችን ሲናገር ትክክለኛ ቃላት ይመርጣል። አንድ ህዝብ በሰላም መኖር እንዲችል መከባበር ምን እንደሆነ አውቆ ማደግ አለበት። መከባበር ምን እንደሆነ ለማወቅ የሶስት ህይወት ደረጃ ተካፋይ መሆን አለብን። ሁለቱ መማሪያ ናቸው። ሶስተኛው መኖሪያ ነው። እንዴት? መጀመሪያ ወላጆቻችን በስርዓት ካሳደጉን ነው። ሁለተኛው ከትምህርት ቤት በጥሩ እውቀት ታንጸን ከጨረስን ነው። ሶስተኛው በተከታታይ በህይወታች ውስጥ ክፉና ደጉን ለይተን መማር ከቻልን ነው። መከባበር ማለት ሌላ ሰው ማክበር ብቻ አይደለም። ለምስሌ አንድ ሰው ታልቁን ማክበር፣ ህግ ማክበር፣ ሴት ማክበር፣ ነጻነት ማክበር፣ ስራ ማክበር፣ ቀጠሮ ማክበር፣ ፈጣሪ ማክበር፣ ሃሳብ ማክበር፣ እውቀት ማክበር ከቻለ ጥሩ ዜጋ ይወጣዋል። በራሱ የሚተማመን ታታሪ ዜጋ ስለሚወጣው የውጭ ሃገራትም ያከብሩታል።

ቤተሰብ በፍቅር ያደገ ርህራሄ ይገባዋል። ከት/ቤት ገንቢ እውቀት የቀሰመ ጠቃሚ ዜጋ መሆን ይችላል። እራሱን ሲችል ደግሞ ሁሉም ነገር ላይ ጥሩ ምክንያት ያለው አስተሳሰብ ያዳብራል። የትውልድ ቦታችን ከተማ ወይም ገጠር ሊሆን ይችላል። ቤተሰብ እንዴት አድርጎ አንዳሳደገን መናገር አልፈልግም። ት/ቤት ገብተን ምን ተምረን እንደወጣን ማወቅ አልችልም። ከቤተሰብ እና ከትምህርት በኋላ የማሰብ አቅማችን እንዴት እንደሆነ ግን መገመት እችላለሁ። ስንቶቹ የኢትዮጵያ ልጆች ፊዴል እንደቆጠሩ በግልጽ አይታወቅም። ሲጃጃሉ ወይም ሲጨክኑ ግን አያለሁ። የሚያጃጅላቸው ሃይማኖት እና ባህሉ ነው። ጨካኝ የሚያደርጋቸው አስተዳደጋቸው ነው። ብዙወቹ የጎደለ ለመሙላት፣ የተጣመመ ለማቃናት እና አዲስ ነገር ለመፍጠር ያላችው አቅም ዝቅተኛ ነው።

ብዙወቹ የጎደለ ለመሙላት፣ የተጣመመ ለማቃናት እና አዲስ ነገር ለመፍጠር ያላችው አቅም ዝቅተኛ ነው።

ምክንያቱም አስተሳሰባችን የተገነባው ሃይማኖት እና ባህል ላይ ያተኮረ በመሆኑ ነው። ሃይማኖት እና ባህል አያስፈልጉም ማለቴ አይደለም። የህይወታችን መመሪያ ግን መሆን አይችሉም። በበኩሌ እምነት ያስፈልገኛል። ምክንያቱም ማታ ተኝቼ ከእንቅልፍ ጧት እንዴት እንደምነቃ በራሴ አላውቀውም። ጥሩ የሆነ ባህል ያስፈልገኛል። ምክንያቱም መሰረቴን መርሳት የለብኝም። ነገር ግን ሁሉንም ሰው ማግባባት የሚችል ሞተር መከባበር መሆኑን ማወቅ ብዙ ችግር ይፈታል።

ሞተሩ ፍቅር እና ክብር ከሚያውቅ ቤተሰብ ይጀምራል። ሞተሩ ት/ቤት ሲገባ በጥበበኛ አስተማሪ ይገጠማል። ሁለቱን ደረጃዎች ካለፈ በኋላ ከህብረተሰቡ ጋር ተግባብቶ ስራ ይጀምራል። ሶስቱም የእውቀት ሰንሰለት ናቸው። የኢትዮጵያ ልጆች የእውቀት ሰንሰለት ግን የሆነ ቦታ ላይ ተበጥሷል። የአንዲት ሃገር እድገት እና ውድቀት በህዝቧ ጭንቅላት አቅም ይለካል። የሚያስብ ጭንቅላት ከሌለን የለንም።

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!