mejemer.com
ቀላል ፍልስፍና

ጀግና በሃሳብ!

mejemer ethiopia hero

ንኛውም ሰው ቢሆን፤ ትርፍ ጊዜውን፤ በከፊልም ቢሆን፤ የረባ ነገር ላይ መጠቀም ይችላል፡፡ ጊዜውን የረባ ነገር ላይ መጠቀም የጀመረ ሰው፤ ስለ ሰው ሳይሆን ስለ ሃሳብ ማውራት ይጀምራል፡፡ እከሌ እንዲህ አለ ብሎ በተደጋጋሚ ስለሰው ማውራት ይቀንሳል፡፡ እራሱን የቻለ አስተሳሰብ ይኖረዋል፡፡ መጥፎ ወይም አደናጋሪ አስተሳስብ በቀላሉ አያሳስተውም፡፡ ባስተሳሰቡ ሞኝ አይሆንም፡፡ ጥያቄ መጠየቅ ይጀምራል፡፡ አዲስና ጠቃሚ ነገር መፍጠር ይችላል፡፡ በቃላት ምክንያት ጠጅ እንደጠጣ ሰው በፍጥነት አይሰክርም፡፡ ያልተጠበቀ ነገር ሲያይና ሲሰማ አይደናገጥም፡፡ ስሜት ውስጥ አይገባም፡፡ ጊዜ ሳያባክን ወዲያውኑ በሃሳቡ መመርመር ይጀምራል፡፡ ጊዜውን ባግባቡ ይጠቀማል፡፡ አስተሳሠቤ ላይ ከፍተኛ የሆነ አቅም አለኝ፡፡ ምንም ነገር አያግደኝም ብሎ ያስባል፡፡

እንጀራ ለመጋገርና የዶሮ ወጥ ለመስራት ብዙ ጊዜ እንጠቀማለን፡፡ እንጀራ የሚወጣው ለ3 ቀናት አካባቢ ተቦክቶ ከቆያ በኋላ ነው፡፡ ዶሮም ተላልጣና ታጥባ 12 ብልት ይወጣታል፡፡ በኋላም በቅመምና በሽንኩርት አብዳ ወጥ እስከሚወጣት ድርስ የሚወስደውን ጊዜ አስቡት፡፡ መጨረሻ ላይም አሳዛኟ ዶሮ ለሽታና ለጣዕም ትተርፋለች፡፡ ሁሉም ነገር ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ለማንኛውም እህል እንጀራ ወጣው፡፡ ዶሮም ወጥ ሆነች፡፡ እኛስ ልክ እንደ ሰው ምን ወጣን? ብሎ ማሰቡ አይከፋም፡፡ ኢትዮጵያ ከ3000 ዓመታት በላይ እድሜ አላት እንላለን፡፡ እስካሁን ድረስ ግን አንድነትና መከባበር ትልቅ ፈተና ሆነውብናል፡፡ ይኸ ምን ያሳየናል? ምን ያስተምረናል? ችግሩ ምንድነው? እኔ እንደሚመስለኝ፤ ማሰብ አቅቶን ሳይሆን፤ የማሰብ አቅማችን ላይ፤ ትኩረት ለመስጠት፤ ጊዜ ስለማንጠቀም ነው፡፡

በነገራችን ላይ፤ አንድነት ማለት፤ አንድ አይነት መሆን አይደለም፡፡ አንድነት ማለት፤ በመከባበር መንፈስ፤ በልብና በአዕምሮ፤ መዋሃድና መስማማት መቻል ማለት ነው ብየ አስባለሁ፡፡

ሳባችን ላይ የምግቡን አሰራር ያህል ጊዜ ብንጠቀም ኖሮ ብዙ እርቀን መሄድ ይቻል ነበር፡፡ ለሰው ልጅ ህይወት የምናሳየው ደንታ ከፍተኛ ይሆን ነበር፡፡ ረጋ ብሎና ጊዜ ተጠቅሞ ማሰብን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ለዚህም ነው መናገርና ማድረግን ከሁሉም በላይ መርጨ ያነሳኋቸው፡፡ ብዙ ሁነታዎች ላይ አብረው ይሄዳሉ፡፡ ይኸ እንዳለ ሆኖ ደግሞ ሰዎች ነንና ሁሉም ነገር ፍጹም አይሆንም፡፡ ስለዚህ ምናልባት ያልኩት ነገር ተሰሚነት ባያገኝም ነጥብ አለው፡፡ ያደረኩት ነገር ተቀባይነት ባይኖረውና ባያኮራኝም አላፍርበትም ብሎ ማሰብ የተሻለና የበለጠ እንዲናደርግ ያበረታታናል፡፡ ለምሳሌ አሁን እኔ ዛሬ የምናገረው የዛሬው ማንነቴ ነው፡፡ ወደፊትም ቢሆን መሰረታዊ ነገሩ ብዙ እንደማይቀየር ይሰማኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ነገ ወይም ከአመታት በኋላ፤ ተመልሼ ሳየው አሳፋሪ ሆኖ እንዲጠብቀኝ በጭራሽ አልፈልግም፡፡ የዚህ አይነት አስተሳሰብ እራሴን ለበጎ ነገር ለማዘጋጀትና ለማዘዝ ያነቃቃኛል፡፡ ባጭሩ አባባል በተቻለ መጠን እርሴን አርማለሁ፡፡ እራሴን እቆጣጠራለሁ ለማለት ነው፡፡ እራሴን ለማረምና ለመቆጣጠር የማደርገው ጥረትና የማሳየው ፍላጎት፤ መብቴን ይጋፋዋል ብዬ አላስብም፡፡

እንደምታዩት በየቀኑ ከበቂ በላይ ጊዜ አለን፡፡ ያለውን ጊዜ ለመጠቀም ግን ልባዊ ፈቃድ ይፈልጋል፡፡ ጊዜው እኮ ይበራል ማለት የተለመደ ነው፡፡ ግዜ ስለማይቆም ይኸ አባባል ትክክል ነው፡፡ ጊዜውማ አሳምሮ ይበራል፡፡ በተለይ ደግሞ የረባ ነገር አድርገን ጊዜአችንን እንዴት እንደተጠቀምንበት ማሳያና ማስታወሻ ከሌለን ግዜው በፍጥነትና በከንቱ ያልፋል፡፡ ባጠቃላይ ጊዜያችንን ረጋ ብለን በትክክል እንጠቀምበት ማለቴ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ጠንካራ የሆነ አስተሳሰብ ያላቸው ሰወች እንዲባዙ ትፈልጋለች፡፡ ይኸን ለማሳካት ደግሞ አቋራጭ መንገድ የለም፡፡ ያስቡበት!!

ከታች አስተያየት ይስጡ

* መጻፍ ያለበት
2000

የተሰጡ አስተያየቶች

አስተያየት ገና አልተሰጠበትም። የመጀመሪያው ይሁኑ!