አስታውስ ተለማመድ
tatariw
Mon, 12/26/2022 - 10:27

# አስታውስ፤
የሃሳብ አቅጣጫ እና ብርሃን ብታሳይ ሰነፎች መራመድና ማየት አይፈልጉም። መልካም ብትሆን ክፉዎች ሊጠሉህ ይችላሉ። አዋቂ ብትሆን አላዋቂዎች ክብራቸው ስለሚነካ ላይፈልጉህ ይችላሉ። ብሄራዊ ራዕይ ቢኖርህ ጠባቦች አርቀው ማሰብ ይሳናቸዋል። ጠንካራ አስተሳሰብ ሲኖርህ ሰወች ግር ሊላቸው ይችላል። የተለየ ሃሳብ ብታፈልቅ ከባህል፣ ከአስተዳደግ እና ከውሎአቸው ስለሚለይ ጥፋተኛ ሊያደርጉህ ይችላሉ። ሁሉንም ሰው ማስደሰት አይቻልም።
# ተለማመድ!
ሃሳብህ ሰወችን ለማስደሰት ሳይሆን ጥያቄ የሚያስነሳ ከሆነ ከፍተኛ ሚዛን አለው። አሳታፊ እና የጋራ ጥያቄ ላይ አተኩር። የችግር አባባሽ ሳይሆን የመፍትሄ አካል ያደርግሃል። አዲስ ሃሳብና ጥያቄ ያጀግናል! ልብ የሚሉ ያውቁታል። ያኔ ሰወች ሃሳብህን ባይቀበሉትም አንተን ግን አይንቁህም። ከመናቅ በታች የወረደ ህይወት የለም። ትካሻህ ከፍ፣ አንገትህ ቀና፣ ፊትህ ዘና፣ ሃሳብህ ልዩ እና አሳታፊ መሆኑን ሁል ጊዜ አስብበት። ደስ የሚሉ ቃላት ላይ ሳይሆን መፍትሄ የሚያፈልቁ ተግባራዊ ቃላት ላይ አተኩር። ሁል ጊዜ የምታውቀው እና የለመድከው ሃሳብ የማይሰራ ከሆነ ችክ አትበል። ለምሳሌ አንድ የሚያምር እና የምትወደው ጥቁር ቀለም ያለው ሸሚዝ አመቱን ሙሉ አይለበስም። ይሰላቻል። ሌሎችም ቀለሞች አሉ። ሞክራቸው። ሃሳብም እንደዛው ነው።
አስተያየት ካለዎት ከታች ይስጡ። አመሰግናለሁ!
Add new comment