ቀና ብለህ እየው ልጄ ነው ይበልህ!

ሰበብ እያበዛህ፣
መዘምን አለፈህ፣
መሰልጠን ቀረብህ፣
እሱ ያውቃል ብለህ፣
አንገትህን ደፍተህ፣
አይንህን ጨፍነህ፣
አዕምሮህን ዘግተህ፣
ልብህንም ደፍነህ፣
ምንም አይታይህ፣
ወደታች እያየህ፣
ክፉና በጎውን መለየት አቅቶህ፣
የሰነፈው ባህል እንዲህ ጠልፎ ያዘህ፣
ወይ ባስተሳሰብህ፤ ወይ ባስተዳደግህ፣
ፊትህን ደብቀህ፣
እንዴት አርጎ ይስማህ፣
እንዴት አርጎ ይይህ፡፡
ቀና ብለህ እየው፣
ባየሩ በጉሙ ሲንሳፈፍ ካየኸው፤
ያንተ ልጅ ነኝ በለው፤
ሰበበኛ እንዳልሆንክ ወስነህ ንገረው፣
ሌላ ጊዜም ቢሆን እንዳታስቸግረው
መልሱንም አዳምጠው፡፡
ድርሻና ሚናህን ያኔ ታውቀዋለህ፣
ቀና ብሎ ማየት ትለማመዳለህ፣
በራስህ መወሰን ድፍረት ታገኛለህ፣
ብቻህን እንደሆንክ ምልክት ታያለህ፣
ከራስ በላይ ንፋስ መሆኑን ታውቃለህ፣
አይደፋ አንገትህ፣
ቢሆንም ላባትህ፣
ቀና ብለህ እየው ፈጣሪህ ይኩራብህ፤
ልጄ ነው ይበልህ፣
ከሰማና ካየህ፡፡
እንኳን አደረሰሽ 365!

እንኳን አደረሰሽ 365፣
ምንድነው የኔ እድገት?
ትምህርት ለመውሰድ ካለ ያጠፋሁት፣
ገትሮ ለመያዝ ካለ ያለማሁት፣
በጎ ወይስ መጥፎ ካፌ ያወጣሁት?
ሰው ስለመሆኔ ምንድነው ያሰብሁት?
ዝም ብዬ እያየሁ ባሪያ የሆንኩበት፣
ወይም ወገኔ ላይ ጨካኝ የሆንኩበት፣
ቀና ሃሳብ ካለኝ ለማሳየት ውጤት፣
አንድ ሁለት ብዬ የሚቆጠር ስኬት፣
ምን እንደሰራሁኝ ልኩን የማይበት፣
ውሸት የሌለበት፣
መጀመሪያ ክብር ስለ ሰው ልጅ ህይወት፣
መከበር ከፈልግሁ በሰፊው ህዝብ ፊት፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!
ኮተት ያልበዛበት
Add new comment