Skip to main content
ቆንጆ አስተሳሰብ እንዴት ይሰራል?
ለሚሰሩ እጆች፣ ለሚወዱ ልቦችና ለሚያስቡ አዕምሮዎች፤ መጀመር

አሁን ወይም በጭራሽ፤ ዲያስፖራ እንጀራ ክፍል 1

mejemer fantaw injera Ethiopia Amharic Tatariw mejemeriya Addis Ababa amharic Fantaw Tesema

አሁን ወይም በጭራሽ፤ ዲያስፖራና እንጀራ፡፡ ክፍል 1

አገር ቤት ወደ ውጭ ሃገር፤ ምግብ ለምን እንደሚወጣ ለብዙ አመታት ሲያንገበግበኝ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ብታምኑም ባታምኑም፤ አንዳንድ ስብሰባዎች ላይ ጉዳዩን አንስቼ አውቃለሁ፡፡ በጽሁፍ በማቅረብ ሞክሬ ነበር፡፡ ለማውቃቸው ሰዎችና ጓዴኞቼ ነግሬያቼው ነበር፡፡ ሃሳባቸውን ለማወቅ ጠይቄያቼው ነበር፡፡ ምንም ለውጥ አላመጣም፡፡ ከ 5 አመታት በፊት አካባቢ ደግሞ፤ ዩቱብ ላይ በቪዴዎ ተዘጋጅቶ ቀርቦ ነበር፡፡ የረባና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ሳይገኝ ቀረ፡፡ ሃሳቡ ትክክልና የሚሰራ ሆኑ ቢታይም በቂ ድጋፍ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር ግን የለም፡፡ ለምን ብትሉኝ እስካሁን ድረስ ልክ እንደ ቁጥር 3 እና 1፣ 8 ሲካፈል ለ2፤ 6 ሲቀነስ 2፤ 2 ሲባዛ በ2 መሆኑ በትክክል እንደሚታወቀው ሁሉ፤ ሃሳቡ ላይ ምንም ስህተት አላገኘሁም፡፡

ፈልጌ፣ ገልጌ፣ ፈልጌ ስህተት ማየትና ማግኘት አልቻልኩም፡፡ አሁን እንደገና አቀራረቡ ተሻሽሎ፤ የደረስኩበትን ሃሳብ ለማስተዋወቅ ነው፡፡ እመኑኝ፤ ስራ ላይ ከዋለ ለሁላችንም የሚጠቅም ሃሳብ ነው፡፡ በተለይ ባሁኑ ጊዜ፤ ወገኖቻችንን ለመርዳት፤ ተፈላጊ የሆነ ሃሳብ ነው፡፡ ምንም አይነት ዋጋ አይጠይቅም፡፡ ምንም አይነት ገንዘብ አያስከፍልም፡፡ ምንም አይነት ጊዜ አይሻማም፡፡ ምንም አይነት ጉልበት አያባክንም፡፡ ምንም አይነት መስዋዕት አይጠይቅም፡፡ እንዳውም በነጻ ነው፡፡ አይደለም ለምግብ ለኢትዮጵያ ብለው ለህይወታቸው ምንም የማይሳሱ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ይኸን የማያውቅ አለ? ግን አገር ቤት ነው ያሉት፡፡

ለባህል ምግብና ፍላጎታችን አማራጭ አለን!

ያስፖራው ከተባበረ በቀላሉና በነጻ ሃገር ቤት ለሚኖሩት ወገኖቻችንን በምግብ መርዳት ይቻላል፡፡ ገንዘብ ካዋጣን በኋላ ወደ አገር ቤት እንደምንልክ ይታወቃል፡፡ በግላችንም እንረዳለን፡፡ ሌላ ተጨማሪ እርዳታም ማበርከት ይቻላል፡፡ ሰውን ለመርዳት አይነቱና መንገዱ በጣም ብዙ ነው፡፡ አሁን የባህል ምግብና ፍላጎታችን እንዴት ሊሆን እንደሚችል ባጭሩ ላስረዳ፡፡ እዚህ ንግግሬ ላይ እንጀራ ብጠቀስም፤ ሁሉንም አይነት ጥሬና የበሰለ የባህል ምግብ ይመለከታል፡፡ ለምሳሌ እንጀራ፣ በርበሬ፣ ቆጮ፣ ቅመም፣ ዱቄት፣ ቂቤ፣ ቆሎ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ የሚወጣ ማንኛውም አይነት ምግብ ማለቴ ነው፡፡ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ይመለከታል፡፡ የባህል ምግባችን ሊያምረን ይችላል፡፡ ሊናፍቀን ይችላል፡፡ አምሮትና ናፍቆታችን እንዲወታልን ግን በጣም ቀላል የሆነ ተቀራራቢ መፍትሄ አለው፡፡ ውጭ አገር ውስጥ የተለያዩ የምግብ ምርጫወች አሉን፡፡ እንጀራ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኝ የምግብ መድሃኒት አይደለም፡፡ እዚሁ ውጭ አገር ተመሳሳይ የሆነ ዱቄትና ቅመም ገዝተን የሚጥምና ቆንጆ የሆነ የባህል ምግብ መስራት ይቻላል፡፡ ሁሉንም አይነት የባህል ምግብ ከዚሁ ከውጭ ሆነን ማሰናዳት ይቻላል፡፡ ለግል ፍጆታ ሊሆን ይችላል፡፡ ለንግድና ለድግስ የሚቀርብ ሊሆን ይችላል፡፡ በጋራ ሆነን ወገኖቻችንን እንዴት መርዳት እንደሚቻል ለማሳየት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወደ ሃገርቤት ለጉብኝት ስንሄድ እዛው መብላት ይቻላል፡፡ የባህሉ ምግብ የትም ቢሆን፤ መቼም ቢሆን አይቀርብንም፡፡

አሁን ያለፈው አልፏል፡፡ ወደፊት መሻሻል ይችላል

ውጭ አገር የምግቡ አይነት፣ ምርጫው፣ ብዛቱና ጥራቱ እንደ ልብ ነው፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ የመጣ ምግብ ለመብላት በቂ ምክንያት የለንም፡፡ እንዳውም ጎበዝ ብንሆን ኖሮ፤ ምግብ ወደ ኢትዮጵያ መላክ ነበረብን፡፡ የመላክ ፍላጎትና ትብብራችን ያነሰ ቢሆንም፤ ማምጣትና ማስመጣት አያስፈልገንም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ከባድ የሆነ የምግብ ችግር አለ፡፡ ሃገር ቤት ወገኖቻችን በቂ ምግብ የላቸውም፡፡ ርሃብ አለ፡፡ ምግብ ወደ ውጭ በወጣ ቁጥር እንሱ ዋጋ ይወደድባቸዋል፡፡ ይኸን ለይቶ ለማወቅ ውኋ የመጠጣት ያህል በጣም ቀላል ነው፡፡ ዋናውና ወሳኙ ጥያቄ ግን የቱን ያህል አሳስቦናል? የቱን ያህል ቦታ ሰጥተነዋል? በሚሊዎን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን አሁን እና በቅርቡ ለርሃብ የተጋለጡ ናቸው፡፡ አሁን ለጊዜው በዜና ላይታይ ይችላል፡፡ ረሃቡ ግን ከዚህ በፊትም የነበረና የተለመደ ነው፡፡ ዲያስፖራው የባህል ምግብ የሚፈልገው ጊዜያዊ አምሮቱን ለመወጣት ነው፡፡ ይኸን ለማሳካት ግን ሌላ አይነት ምርጫ አለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ አንሶና ሰው እየተራበ ከኢትዮጵያ የመጣ ምግብ መብላት ትልቅ ስህተት ነው፡፡

የዚህ አይነት ስህተት የሚሰሩ ከሆነ፤ ምናልባት ሊሰማዎት ይችላል፡፡ ሊያሳፍረዎት ይችላል፡፡ ጥሩ ስሜት ላይሰጥዎት ይችላል፡፡ ልብ አላሉት ይሆናል፡፡ በደንብ አላሰቡበት ይሆናል፡፡ አሁን ግን ያለፈው አልፏል፡፡ ለወደፊቱ ግን ሁላችንም ተባብረን መሻሻል እንችላለን፡፡ ከአገር ቤት የመጣ ምግብ የማይበሉ ከሆነ ደግሞ፤ ሰው መሆን ማለት ያየውንና ያገኘውን፤ መብላት ብቻ እንዳልሆነ ደርሰውበታል፡፡ ይኸ ሞራል የሚባለው ነገር ምን ማለት እንደሆነ ደርሰውበታል፡፡ የዚህ አይነት አቋምና ባህሪ በጣም የሚያኮራ ስለሆነ፤ እንኳን ደስ አለዎት! እውነቴን ነው!

ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚወጣው ምግብ ብዛት፤

ኢትዮጵያ የሚወጣውን ምግብ ብዛት ሲያስቡት በጣም ያስደነግጣል፡፡ ብዙ ምግብ ከኢትዮጵያ ወደውጭ ይወጣል፡፡ ወደ አረብ ሃገር፣ ወደ አውሮፓ፣ ወደ አሜሪካ፣ ወደ አፍሪቃ የመሳሰሉት ሃገራት፤ ለዲያስፖራው ፍጆታ ሲባል ምግብ ከኢትዮጵያ በገፍ ይወጣል፡፡ በብዙ ሺህ ቶን የሚቆጠር ምግብ ከኢትዮጵያ ይወጣል ብየ እገምታለሁ፡፡ ይኸን ምግብ እንዳይወጣ እኛ ከተውነው እዛው ይቀርና እዛው ወገኖቻችን ይበሉታል፡፡ የሚሸጥበት ዋጋ ደግሞ፤ ለውጭ ገበያ ስለማይታሰብ ወገኖቻችን ዋጋ አይወደድባቸውም፡፡ ብዙ ዲያስፖራዎች የራሳቸውን ፍላጎት ለማርካት፤ የተለያየ ምክንያት ይደረድራሉ፡፡ ባህሌ፣ ልጆቼ፣ ሆዴ፤ ልምዴ፤ ማለት ለምደዋል፡፡ ምክንያታቸው አያልቅም፡፡ ለባህላችሁ፣ ለልጆቻችሁ፣ ለሆድና ለልማዳችሁ የባህል ምግብ ይቅርባችሁ አልተባለም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው አንገብጋቢ የሆነ ጉዳይ ስላለ፤ ወገኖቻችንን ቅድሚያ እንስጣቸው ነው የተባለው፡፡ ዲያስፖራው ደግሞ ሌላ ምርጫ ስላለው የባህሉ ምግብ አይቀርበትም ነው የተባለው፡፡ ከዲያስፖራው የሚጠበቀው ከኢትዮጵያ ምግብ እንዳይወጣ መተባበርና ህብረት መፍጠር ብቻ ነው፡፡ መስዋዕት እንዲከፍል አልተጠየቀም፡፡ ገንዘብ እንዲከፍል አልተጠየቀም፡፡ ጊዜውን እንዲጠቀም አልተጠየቀም፡፡ አንተ ተርበህ ሌላውን መርዳት አለብህ ተብሎ አልተጠየቀም፡፡ ምግቡ እዛው ቀርቶ እንዲበላ በመተው ብቻ፤ ወገኖቻችንን አሳምረን በነጻ መርዳት እንችላለን፡፡ ይኸን በተግባር ለማሳየት፤ እንደጠቀስኩት ጊዜ አይጠይቅም፡፡ ገንዘብ አይጠይቅም፡፡ ስራ አይጠይቅም፡፡ ምንም አይነት ልፋትና መጨናነቅ አያስፈልገውም፡፡ ስማርት አስተሳሰብ የሚባለው ይኸ ነው! ከዚህ የበለጠና የተሻለ በነጻ መርዳት የሚያስችል መንገድ አለ? አይመስለኝም፡፡

የልብ ውህደት የአዕምሮ አንድነት

ከምግብ በላይ ደግሞ አገር ቤት ያሉት ወገኖቻችን ምን ያስባሉ መሰላችሁ? አሃ! ለካ ዲያስፖራው ለኛ ያስብልናል ይላሉ፡፡ እንዳሰብንላቸው ያውቁታል፡፡ ምክንያቱም በርቀት አገር ቤት ካሉት ወገኖቻችን ጋር፤
1ኛ) በልባችን ተገናኝተን እንዋሃዳለን፡፡
2ኛ) በሃሳባችን ተያይዘን አንድነት እንፈጥራለን፡፡
የልብ ውህደት፤ የአዕምሮ አንድነት የሚባለው ይኸ ነው፡፡ ቋሚና የሚቆይ መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል አስተሳሰብ ይኸ ነው፡፡ የረቀቀና የተባረከ ሰዋዊ አስተሳሰብ ከሚባሉት ውስጥ፤ አንዱ ይኸ መሆን አለበት፡፡ ታሪክ መስራት እንችላለን፡፡

አመሰግናለሁ!

የዚህ አይነት ዝግጂቴ ይቀጥላል፡፡ በክፍል፤ በክፍል፤ በክፍል አድርጌ ለማቅረብ እየሰራሁ ነው፡፡ ይከታተሉ፡፡ ሃሳቡን ከወደዱት ለጓደኞችዎ ያካፍሉ፡፡ አስተያየት ካለ ከታች ማቅረብ ይቻላል፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ መልካም ውሎ! መልካም ምሽት!

Add new comment

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.